ኢትዮጵያ

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት፡- አንቶኒ ብሊንከን

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት፡- አንቶኒ ብሊንከን

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ( ኤ ኤም ኤን) መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም

በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መናገራቸውን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ትናንት ምሽት አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም፤ በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ፍሬያማ ምክክር መካሄዱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሰረተውን የረዥም ዓመታት አጋርነት ለማጠናከር የሚሰሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በኢትዮጵያ አዲስ የመረጋጋትና የሰላም ምዕራፍ መከፈቱን ለአንቶኒ ብሊንከን ማብራራታቸውን አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት መንግሥት በቁርጠኝነት በመሥራት ላይ መሆኑንም ገልጸውላቸዋል ብለዋል አምባሳደር መለስ ፡፡

የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ለማሳለጥ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት የአሜሪካ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መጠየቃቸውን ቃል-አቀባዩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ሁለንተናዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው የሰላም ትግበራ ሂደቱ በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ የበለጠ እንዲጠናከር የአሜሪካ መንግሥት ሁለገብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ለአንቶኒ ብሊንከን ማብራሪያ መስጠታቸውን አምባሳደር መለስ አለም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር በመተባበር በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን፣ የሶማሌላንድ ችግር እንዲፈታ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ተመሳሳይ ጥረቶችን እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።

በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ ሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ለአብነት አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተም ሁሉንም አካላት አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ የሚደረገውን ጥረትን አብራርተውላቸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እያደረገች ያለውን ጥረት አሜሪካ በአድናቆት እንደምትመለከተውና የሚበረታታ መሆኑን መግለጻቸውንም አምባሳደር መለስ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የሚመጡ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗ የሚያስመሰግናት ተግባር መሆኑንም አንቶኒ ብሊንከን መናገራቸውን አምባሳደር መለስ ተናግረዋል ።

ተመሳሳይ ልጥፎች

የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

admin

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የተለዩ 9 ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ራስ ገዝ ደረጃ ለማሻገር እየተሰራ ነው: – የትምህርት ሚኒስቴር

admin

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቢክ ኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ውድድር አሸነፈ።

admin

አስተያየት ይስጡ