ኢትዮጵያ

በፍትህ ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

በፍትህ ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:-አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) ግንቦት 19/2015 ዓ.ም

በፍትህ ዘርፉ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የፍትህ ሚንስቴር በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር የፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ላይ ከፌደራልና ክልሎች የፍትህ ተቋማት ኃላፊዎችና የክልል ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች ጋር ተወያይቷል።

የፍትህ ሚንስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ በፍትህ ዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና በጎ ጎኖችን ለማጽናት ያለመ ነው።

የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ በፍትህ ዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላሉ ተብለው የተለዩ 10 የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም የዘርፉን አመራሮች የማጥራት፤ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግና የወንጀል የአስተዳደር ፍትህ በአዲስ እይታ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እንዲሁም ከክልሎች ጋር የተሻለ ግንኙነት መዘርጋት፣ ተገቢ የማኅበረሰብ ተሳትፎና የዘርፉን አደረጃጀት በማስተካከል ሳቢና ታማኝነት የተቸረው እንዲሆን የማስቻል እርምጃዎች ይገኙበታል ብለዋል።

ፕሮግራሙን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የፍኖተ-ካርታ ዝግጅት እንዲሁም የድርጊት መርሃ ግብር መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

የፍትህ ተቋማት አቅም ግንባታና የአመራሮች ምደባ እንዲሁም ሽግሽግ መደረጉንም እንዲሁ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተዳደራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ በዘርፉ ያለውን ችግር እንዲሁም የሚነሱ ጥያቄችን ለመመለስ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሎችም ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባና በተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አንስተዋል።

በቀጣይም ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ በመጠቆም።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ በበኩላቸው መንግሥት ይህንን ፕሮግራም ለመፈጸም ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ከኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑን አንስተው ለተግባራዊነቱ ርብርብ መደረግ አለበት ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በፍትህ ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ ያሉ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

የዘርፉ ተዋናዮች እርስ በርስ ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ለኅብረተሱቡ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

ተመሳሳይ ልጥፎች

የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

admin

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የተለዩ 9 ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ራስ ገዝ ደረጃ ለማሻገር እየተሰራ ነው: – የትምህርት ሚኒስቴር

admin

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቢክ ኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ውድድር አሸነፈ።

admin

አስተያየት ይስጡ