ኢትዮጵያ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽዖ ያላቸው ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽዖ ያላቸው ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤምኤን) ግንቦት 1/2015 ዓም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ አስተዋጽዖ ያላቸው ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡለትን የሁለት ረቂቅ አዋጆች ሪፖርትና የውሳኔ ኃሳብ መርምሮ አጽድቋል።

ስለ እጽዋት ዘር ለመደንገግ ማሻሻያ የተደረገበትን ረቂቅ አዋጅና የግብርና አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን አዲስ የወጣ አዋጅን ነው ምክር ቤቱ ያጸደቀው።

አዋጆቹ በግብዓት አቅርቦት፣ በተጠቃሚነት፣ ምርታማነትን በማሳደግ በዘርፉ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በመሙላት ለግብርና ምርትና ምርታማነት የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የረቂቅ አዋጆቹን ይዘት፣ ከአስፈላጊነትና ማስተካከያ የተደረገባቸው እንዲሁም አዲስ የተጨመሩ አንቀጽና ድንጋጌዎችን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

ስለ እጽዋት ዘር ለመደንገግ ማሻሻያ የተደረገበት ረቂቅ አዋጅ ለግብርና ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪዎች የጥሬ እቃ አቅርቦትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የነበረውን የሕግ ክፍተት ለመሙላት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

አዋጁ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት የግሉን ዘርፍ በሚያበረታታና የዘር ኢንዱስትሪን ለመገንባት ትልቅ ሚና በሚኖረው መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበታል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ለተጠቃሚዎች ጥራቱ የተረጋገጠ ምርጥ ዘር በአይነት፣ በመጠንና በወቅቱ ለማቅረብ እንዲያግዝ አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበታል ብለዋል።

የግብርና አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን አዲስ የወጣ አዋጅ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮችን ጥቅም ያስከብራል ሲሉ አብራርተዋል።

በአምራችና አስመራች መካከል ፍትሃዊና ጤናማ ግንኙነትን የሚፈጥር፣ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የነበሩ አሰራሮችን ለማስተካከል ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

አርሶና አርብቶ አደሩን ከአስተማማኝ ገዥዎች ጋር በማገናኘት ጠንካራ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩና ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ግብዓቶችን አስመራቹ ተደራሽ በማድረግ የመንግሥትን ጫና ለመቀነስ በአዋጁ ተደንግጓል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት የሚያስችልና ለማምረት የሚያበረታታ አዋጅ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የግል ባለሃብቶች በግብርና ዘርና ማዳበሪያ ምርት እንዲሰማሩ እድል በመፍጠር የግብርና ግብዓት አቅርቦት ችግርን ከመፍታት አንጻር ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በአዋጁ የተቀመጡ መብትና ግዴታዎችን እንዲሁም አጠቃላይ የአዋጁ ይዘት ላይ ለአርሶ አደሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም ረቂቅ አዋጆቹ የሚያስገኙትን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት ሁለቱንም አዋጆች በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ተመሳሳይ ልጥፎች

የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

admin

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የተለዩ 9 ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ራስ ገዝ ደረጃ ለማሻገር እየተሰራ ነው: – የትምህርት ሚኒስቴር

admin

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቢክ ኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ውድድር አሸነፈ።

admin

አስተያየት ይስጡ