ኢትዮጵያ

የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተተገበረ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተተገበረ ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) መጋቢት 29/2015 ዓ.ም
የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተተገበረ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትር ድዔታዋ የጸጥታና የሰላም ሁኔታን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ዓመታት የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር ተደቅኖብን የነበረውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ያስቻለ ሪፎርም እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመጨረሻው ብሄራዊ ሃይላችን ነው ያሉት ሚኒስትር ድዔታዋ ያለጠንካራ መከላከያ ሰራዊት ጠንካራ ሀገርን መገንባት አይቻልም ሲሉ ገልጸዋል በመግለጫቸው፡፡

ሰራዊቱን የተሟላ ስብዕና በማላበስ በሰው ሃይል፤ በቴክኖሎጂ አንዲሁም በሞራል ማጠናከር ዋነኛ ሀገራዊ አጀንዳችን ሆኖ ቆይቷልም ነው ያሉት፡፡

የሪፎርም ስራውን መነሻ በማድረግ ባለፉት አመታት መንግስት የሀገሪቱን ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነቱን በአግበቡ መጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ሰራዊት ለመገንባት የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንደነበሩ ያነሱት ሚኒስትር ድዔታዋ ጥናትን ተከትሎ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የክልል ልዩ ሃይሎች በተለያዩ መዋቅሮች እንዲደራጁ የሚያስችላቸው ተግባራዊ እርምጃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ስራው በጥናትና ቅድመ ዝግጅት ደረጃ ቆየት ብሎ የተጀመረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሀገራዊ ሰላምን በተሟላ ሁኔታ ለማስጠበቅ ዋነኛ ሃላፊነት የተጣለበት መንግስት ይህንን ሃላፈነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በሁሉም ደረጃ የተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች መልዕክት ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን ሚኒስትር ድኤታዋ አስታውሰዋል፡፡

አንድ ጠንካራ የተማከለ ሰራዊት መገንባት አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት የጠቆሙት ሚኒስትር ድኤታዋ የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ በሁሉም ክልሎች ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት የተጀመረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ባሉ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ አስፈላጊነት ላይ ከመግባባት ላይ በመደረሱ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የተሻለ የሰላም ሁኔታ ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸመ የሚያስችል መሆኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስራዎች መጀመራቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በሁሉም ክልል ለሚገኙ ልዩ ሃይሎች መንግስት እውቅና ሲሰጥ መቆየቱን በማስታወስ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ለሀገራቸው ሉዓላዊነት መከበር ብዙ አስታዋጽኦ ሲያደርጉ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ የሚገኘውን የልዩ ሃይል መልሶ የማደራጀት ስራው ምርጫው ሙሉ በሙሉ ተጠብቆለት ፍላጎቱ ተከብሮለት እንዲተገበር መንግስት አማራጮችን አስቀምጧል ነው ያሉት፡፡

በመልሶ ማደራጀት ስራው በየትኛውም ክልል የሚገኙ የልዩ ሃይል አባላት የኢትዮጵያ የህልውና ምሰሶ ወደሆነው የጀግናው መከላከያ ሰራዊት መቀላቀል አንደኛው አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም ትልቅ ሀገራዊ ጥሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ባለበት ክልል ያለውን የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ ማስጠበቅ እንዲቻል የክልሉን ነዋሪዎች ማገልገል የሚችልበት እድል የሚሰጥ የክልሉን የፖሊስ ሃይል መቀላቀል ሁለተኛው አማራጭ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ አማራጮች ውጪ ወደ መደበኛ ኑሮ መመለስ የሚፈልግ አካል ካለ ሙሉ መብቱ ተጠብቆለት የሚከናወን መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህም የመቋቋሚያ አስፈላጊ ድጋፎች ለማድረግ በመንግስት በኩል ሙሉ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት ሚኒስትር ድዔታዋ፡፡

ተመሳሳይ ልጥፎች

የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

admin

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የተለዩ 9 ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ራስ ገዝ ደረጃ ለማሻገር እየተሰራ ነው: – የትምህርት ሚኒስቴር

admin

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቢክ ኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ውድድር አሸነፈ።

admin

አስተያየት ይስጡ