ኢትዮጵያ

የዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት /ፊያታ/ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ በዘርፉ ጥሩ እመርታ ለማሳየቷ አመላካች ነው – ዶክተር አለሙ ስሜ

የዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት /ፊያታ/ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ በዘርፉ ጥሩ እመርታ ለማሳየቷ አመላካች ነው – ዶክተር አለሙ ስሜ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) ሀምሌ 22/2015 ዓ.ም

የዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሸን /ፊያታ/ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ በዘርፉ ጥሩ እመርታ ለማሳየቷ አመላካች መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሸን /ፊያታ/ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ ይህ ጉባዔ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን ገልፀዋል፡፡
የጭነት ማስተላለፉ ለአገር ኢኮኖሚ ግብዓትና ሸቀጦችን ወደ ገበያ ለማቅረብም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ይህ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄዱም ኢትዮጵያ በዘርፉ ጥሩ እመርታ እያሳየች መሆኑን እንደሚያመላክት ገልፀዋል፡፡
ከውይይቱም በጭነት ምልልሱ የሚታዩትን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማመላከትን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ የበኩሏን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከዓለም አቀፍ ተመሳሳይ ተቋማት ጋርም በጋራ ለመሥራት ፍላጎቷ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዓለም አቀፍ የጭነት አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን 100ኛ ዓመት በዓልን እ.ኤ.አ በ2026 በኢትዮጵያ እንዲያዘጋጅ ጥያቄ መቅረቡንም ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ስቴፈን ግራበር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ የሚባሉ ሥራዎችን መሥራቷን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ዘርፉ ይበልጥ እንዲጠናከርም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጭነት አስተላላፊዎች አገልግሎት ማኅበር የቦርድ ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት ውብሸት፤ ጉባዔው በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ የአፍሪካ አገራት ያላቸውን ፍላጎት በተገቢው ሁኔታ ለማሳካትና አሠራር ለማመቻቸት እንደሚረዳ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢው አገራት በአየር ጭነት ትራንስፖርት ያላትን ስትራቴጂካዊ ሚና ለማስገንዘብ መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2026 የዓለም የዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት ፌዴሬሽን የ100ኛ ዓመት በዓልን ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከማድረግ አንፃርም የዚህ ጉባዔ መካሄድ ሰፊ እገዛ እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ከሦስት ዓመት በኋላ ለሚካሄደው 100ኛ ዓመት ጉባዔ የዓለም አገራት የሎጂስቲክስ ማኅበራት ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ2 ሺህ 500 በላይ እንግዶች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ማኅበሩ በትናንትናው ዕለት በዓለም ዕቃ አስተላላፊዎች ማኅበራት በኩል ሥልጠና ለወሰዱ 28 ኢትዮጵያውያን የምስክር ወረቀት መስጠቱ ይታወቃል።

ተመሳሳይ ልጥፎች

የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

admin

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የተለዩ 9 ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ራስ ገዝ ደረጃ ለማሻገር እየተሰራ ነው: – የትምህርት ሚኒስቴር

admin

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቢክ ኢትዮጵያ የተዘጋጀውን ውድድር አሸነፈ።

admin

አስተያየት ይስጡ