ለአፍሪካ ችግሮች አህጉር በቀል መፍትሔዎች

You are currently viewing ለአፍሪካ ችግሮች አህጉር በቀል መፍትሔዎች

 የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን የሚፈቱት አፍሪካውያን ወገባቸውን አስረው ዘላቂ ልማት ላይ መስራት ሲችሉ ነው-የፓን አፍሪካኒዝም ተመራማሪዋ ሬሞፊል ሎባኬንግ

አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካዊ ችግሮች የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የፖለቲካ ደርዝ ይዞ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1990ዎቹ መጀመሪያ ብቅ ያለው በጋናዊው ጆርጅ አይቲ አማካኝነት ነበር፡፡ ጆርጅ አይቲ ደራሲ፣ የፖለቲካ ተመራማሪና የፍሪ አፍሪካ ፋውንዴሽን በዋሽንግተን ዲሲ ፕሬዝዳንት ናቸው። የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈቱ ብርቱ ጥረት ያደረጉ ሰው እንደሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካዊ ችግሮች የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ለፖለቲካው ዓለም ከተዋወቀ በኋላም በመንግሥታት መሪዎች፣ በፖሊሲ አውጪዎችና በፖለቲካ ምሁራን መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። “አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካዊ ችግሮች” ሲባል ምን ማለት ነው? ምን ያህልስ ወደ መሬት ወርዷል? እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ተቋማትና አባል አገራቱ ለውጤታማነቱ ምን ጥረት እያደረጉ ነው? የሚሉና መሰል ጉዳዮች ደግሞ መነጋገሪያ አጀንዳዎቹ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ማጠንጠኛም እነዚህን ጉዳዮች መዳሰስ ይሆናል፡፡

ጋናዊው ጆርጅ አይቲ እንደሚሉት “አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካዊ ችግሮች” ጽንሰ ሀሳብ በመጀመሪያ የአፍሪካ መንግስታት በአህጉሪቱ ውስጥ ላሉ ችግሮች የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንዲያስወግዱ ጥሪ ማቅረብን ያለመ ነበር፡፡ ይሁንና ከእርሳቸው አስቀድሞም ቢሆን እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ በአፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ በወጡበት ወቅት እንደ ጋናው ክዋሜ ንክሩማህ ያሉ የአፍሪካ ፀረ-ቅኝ ገዥ መሪዎች ለአፍሪካ የጸጥታ ችግሮች በአህጉራዊ የጸጥታ ዝግጅቶች የአፍሪካ ክልላዊ ምላሾችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ታግለዋል ይላል በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረገው ብሩክ ከድር፡፡

በእርግጥ ጽነሰ ሀሳቡ የፖለቲካ ደርዝ ይዞ ከቀረበ በኋላ ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሄዎች መርህ እየጎለበተ ስለመምጣቱ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህም ዋቢ አድርጎ አጥኚው ብሩክ የሚጠቅሰው እ.ኤ.አ በ2013 በላውሪ ኤን “African Solutions to African Problems: South Africa’s Foreign Policy” በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጥናት ነው፡፡ ጽንሰ ሀሳቡ ምን ያህል እየጎለበተ መጣ? ምን ውጤትስ አስገኘ? ምንስ ፈተና ገጠመው ወደሚሉት ጉዳዮች ከመግባታችን አስቀድመን አፍሪካ ለራሷ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት ሲሳናት ምን ገጠማት? የሚለውን ጉዳይ አብነት ጠቅሰን እንፈትሽ፡፡ ለዚህም ከ1967 አንስቶ ለሶስት ዓመታት የቆየው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ እርስ በእርስ ጦርነትን በአስረጅነት እናንሳ፡፡

አፍሪካውያን ከቅኝ ገዢዎቻቸው እቅፍ ወጥተው ዳዴ ማለት እንደጀመሩ እርስ በእርስ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ውስጥ ያለፉ አገራት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ አንዳንድ አገራት ጉዳያቸውን በጠርጴዛ ዙሪያ ከብበው ከመፍታት ይልቅ ጦርን ሲያስቀድሙ የውጪ ኃይሎች እጃቸውን በማስገባታቸው ዜጎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለዘጠና ዓመታት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ውስጥ ቆይታ በማግስቱ ወደእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የገባችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ሁነኛ ምስክር ናት፡፡

ከፈረንጆቹ 1967 አንስቶ ለሶስት ዓመታት ገደማ በቆየው ጦርነት ወቅት የውጭ ኃይሎች ጥቅማቸውን እያነፈነፉ ይበጁናል ላሏቸው ቡድኖች ጎራዴ እያቀረቡ ለግጭቱ መባባስ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ጥቅማችን ይነካል ያሉ አገራት የጦር መሳሪያ እስከ ማቅረብ የደረስ ቀጥተኛ ተሳትፍ አድርገዋል፡፡

በወቅቱ ታዲያ የናይጄሪያ ቀውስ ለአፍሪካ ህብረትም ይሁን ለአፍሪካ አገራት ሰጥቶት ያለፈው ትምህርት ቀላል አልነበረም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ “ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔዎች” ማዕቀፍ ከመነሻ ዓላማው በላይ አድማሱ እየሰፋ መጥቷል፡፡ በዋናነት በኢኮኖሚ ልማት፣ በማህበራዊ ትስስር ዕድገት እና ቀስ በቀስ በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት አህጉራዊ ዘዴዎችን መተግበር የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት እያገኘ ቀጥሏል፡፡

ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሄዎች ሀሳብ በጊዜ ሂደት ተቀባይነት ለማግኘት የውጭ አካላት ጣልቃ ገብተው ካደረሱት ጉዳት በተጨማሪ ሌሎችም ምክንያቶች መነሳት አላባቸው የሚሉት ደግሞ ‘Conflic in the Eastern Nile; The role of business’ መጽሐፍ ደራሲዋ ራዊያ ቶፊቅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የልዕለ ኃያላን አገራት ቸልተኝነት ምክንያት በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ መቀነስ እንደዚሁም የሶማሊያ ቀውስና የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ግጭት ወቅት ፈጣን ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው አፍሪካ ችግሮቿን ለመፍታት የግዴታ ወደራሷ መመልከት አንዳለባት ምልክት የሰጡ ነበሩ ይላሉ ራዊያ ቶፊቅ።

የአፍሪካ ህብረት ምስረታ በራሱ በትክክል ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ለማግኘት ያለመ ነበር የሚሉት ደግሞ በካምፓላ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና የህዝብ አስተዳደር ክፍል መምህሩ ካሳጃ ፊሊፕ አፑሊ (ዶ/ር) ናቸው። የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል፣ አህጉራዊ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እና ተዛማጅ የጸጥታ ተቋማትን በአፍሪካ ህብረት የመመስረታቸው ጽንስ የሚጀምረውም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ከሚለው ሀሳብ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በቅርብ ዓመታት ውስጥም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ያሳዩት ተግባራዊ እንቅስቃሴም ሌላኛው አድናቆት የሚቸረው ተግባር ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ ለዚህም አስረጅዎችን እንጥቀስ፡፡ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የቆየው የሦስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት እንዲካሄድ ይዘውት የነበረው የጸና አቋም ኢትዮጵያ ለህብረቱ ያላትን ክብርና እውቅና የሚያሳይና የሚደነቅ ነበር፡፡ እንደ አረብ ሊግ ያሉ ተቋማት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ለመግባት በሞከሩበትም ወቅት ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚነሱ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈታ የምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለአፍሪካውያን አብሮነት መጠናከር እንዲሁም ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ ወቅት የኅብረቱ ልዩ ተወካይ በሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኩል ጦርነቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እልባት እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር።

በወቅቱም የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ጦርነቱ የተፈታበት ሂደት ለመላ አፍሪካውያን ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሰላም ሂደቱ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ የተከተለ ስለመሆኑና በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያሳዩትን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውም የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ወቅትም ያነሱት አንኳር ነጥብ እኛ አፍሪካውያን ለችግሮቻችን አናንስም የሚል ነበር፡፡ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን እሳቤ ግጭትን ከመፍታት ባሻገር የአህጉሪቷን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ መጠቀም ይገባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአፍሪካ ህብረት ባለፉት ዓመታት አህጉሪቷን የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ለአፍሪካዊ ችግሮቻችን አፍሪካዊ መፍትሄ ከማበጀት አንጻር ከፊታችን ብዙ ይጠብቁናል ነው ያሉት፡፡

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ከመስጠት አንጻር የአፍሪካውያን ቀሪ የቤት ስራ ሰፊ ነው። ቀሪ የቤት ስራውን በተመለከተና ጽንሰ ሀሳቡንም መሬት ላይ ለማውረድ ፈተናዎቹ ምንድናቸው? ለሚሉት ጉዳዮች ደግሞ የፓን አፍሪካኒዝም ተመራማሪዋ ሬሞፊል ሎባኬንግ ‘African Solutions to African Problems: A Viable Solution towards a United, Prosperous and Peaceful Africa’ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ምላሽ አላቸው፡፡

ሬሞፊል ሎባኬንግ እንደሚሉት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ማዕቀፎች ቢኖሩም፣ ስምምነቶቹን በተግባር ለማዋል የአፍሪካ መሪዎች የቁርጠኝነት ክፍተቶች አሉ። በውጫዊ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆን የአፍሪካ ህብረት የለጋሾችን ፍላጎት እንዲቀበል ያደርገዋልና አፍሪካውያን ወገባቸውን አስረው ዘላቂ ልማት ላይ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። በሌላም በኩል በአፍሪካ መንግስታት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመተማመን ለጋራ ጥቅም በአንድነት ለመቆም ዋነኛ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል ይላሉ፡፡

በዚህም ሳቢያ የአፍሪካ ህብረት በየወቅቱ በግማሽ ልብ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉንም ተመራማሪዋ ሬሞፊል ሎባኬንግ ጠቅሰው፣ የአንዳንድ አፍሪካ አገራትን ጉዳይ በአስረጅነት ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ በኮትዲቯር እና በሊቢያ የተከሰቱት ቀውሶች የአፍሪካ ኅብረት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እንደነበር ያነሳሉ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review