አፍሪካ -በኪነ-ጥበብ

You are currently viewing አፍሪካ -በኪነ-ጥበብ

AMN-የካቲት 7/2017 ዓ.ም

አፍሪካ የስልጣኔ ምንጭ የብዙ ድንቅ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት፣ ምድረ ገነት መሆኗን የሚያሳዩ የኪነጥበብ ስራዎችን በተለይም ፊልሞችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መመልከት ጀምረናል። ለአብነት ያህል ብላክ ፓንተር (2018) – ምናባዊ ዋካንዳ አፍሪካን በቴክኖሎጂ የላቀች እና ጠንካራ ሀገር እንደሆነች የሚያሳይ ፊልም ነው።

“The Boy Who Harnessed the Wind (2019) ” በማላዊ መንደሩን ከረሃብ ለመታደግ የንፋስ ተርባይን ስለሰራ የማላዊ ልጅ ጠንካራ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ፊልም ነው ።ይህም የአፍሪካን ብልህነት እና ጽናት ያሳያል።

“Queen of Katwe (2016) “በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ይህ ፊልም ከካትዌ ሰፈር ውስጥ የወጣችውን ወጣት ኡጋንዳዊ ልጃገረድ ተከትሎ የቼዝ ሻምፒዮን ስትሆን ያሳየናል። ፊልሙ የአፍሪካውያንን ተሰጥኦ፣ ቁርጠኝነት እና የትምህርት ሃይል አጉልቶ ያሳያል።

አብዛኞቹ ተፅዕኖ ፈጣሪ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ግን አፍሪካውያን የአውሮፓ ጣልቃ ገብነት ወይም ስልጣኔ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ሀሳብ በማጠናከር አፍሪካን እንደ “ጨለማ አህጉር”፣የአደጋ እና አረመኔያዊ ቦታ አድርገው ይገልጿታል።

የአውሮፓ ፊልሞች አፍሪካን እና አፍሪካውያንን በታሪክ የሚወክሉባቸው አንዳንድ ቁልፍ መንገዶች ሲል የታሪክ ተመራማሪ የሆነው ሚካኤል ማሀባዲ “media representation of Africa “በሚል ጥናቱ ያስቃኘናል። በጥናቱ ከጠቆማቸው ጉዳዮች መካከል ብዙ ቀደምት ፊልሞች አፍሪካውያንን እንደ ትንሽ ጎሳ፣ ሥልጣኔ የሌላቸው፣ ወይም ምሥጢራዊ ፍጡራን አድርገው ይገልጹ ነበር።

ብዙውን ጊዜ የአምልኮ ሥርዓቶችን፣ የዱር መልክዓ ምድሮችን እና “ልዩ” ባህሎችን ያጎላሉ። ለአብነት ያህል አፍሪካ በዱር አራዊትና ጥንታዊ ጎሣዎች የተሞላ ጫካ የምትታይበት የታርዛን ፊልሞችን ያካትታል።

የአውሮፓ ፊልሞች ነጭ ተዋናዮችን ህዝቡን ከጦርነት፣ ከድህነት፣ ወይም ከራሳቸው አላዋቂነት “ለመታደግ” ወደ አፍሪካ የሚመጡ ጀግኖች አድርገው ይቀርባሉ እንደ “የአፍሪካ ንግስት” (1951) ያሉ ፊልሞች ደግሞ ይህንን እሳቤ ያንፀባርቃሉ።

አሁን ባለንበት ዘመንም አፍሪካ በምእራባዊያን ኪነጥበብ በተለይም በፊልሞች እና በሙዚቃ ክሊፓች በሚገባት ልክ አልተገለጸችም ሲል በሙዚቀኛነቱ እና በአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ጉዳይ ተቆርቋሪነቱ የሚታወቀው አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ከኤ ኤም ኤን ኤፍ ኤም 96.3 ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

ኪነጥበብ የማስተማር፣ የማዝናናት ብሎም መልእክት የማስተላለፍ ሀይል አላት ። ይሁን እንጅ በአለም ላይ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ስራ የሚሰሩት ምእራባውያን አፍሪካን እነሱ ሊገልፁ በፈለጉት ልክ እንጅ ትክክለኛውን ማንነቷን ገልፀውታል ብየ አላስብም ሲል ያክላል አርቲስቱ።

አፍሪካውያን ተዝቆ የማያልቅ እምቅ ሀብት ብሎም እነ ቦብ ማርሊንን የመሰሉ ለአለም አንድነትን ሰብከው ያለፉ በአለም ህዝብ ልብ ሁሉ አሻራቸውን ያኖሩ ጥበበኞች ምድር እንደመሆኗ በዚህ ዘመንም የምንገኝ አፍሪካውያን የኪነጥበብ ባለሙያወች በስራችን ታላቋን አፍሪካ ታሪኳን ለትውልዱ በተገቢው መንገድ የማስተላለፍ ሀላፊነት አለብን ሲል ገልጿል።

በቤቴልሔም አየነው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review