በወለጋ ልማት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን አይተናል-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

You are currently viewing በወለጋ ልማት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን አይተናል-የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

AMN – የካቲት 16/2017 ዓ.ም

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በነቀምቴ ከተማ በብልጽግና ፓርቲ ሑለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች እና አቅጣጫ ላይ ከአራቱም ወለጋ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የነቀምቴ ከተማ እና የምስራቅ ወለጋ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በውይይቱም ሆነ በጉብኝቱ የወለጋ ሕዝብ እና አካባቢው ባለፉት ዓመታት የታጠቁ ኃይሎች ካደረሱት ጉዳት አጋግሞ በቁጭት እና በእልህ ወደ ተሟሟቀ የልማት እንቅስቃሴ መግባቱን ተገንዝበናል ብለዋል።

ወለጋ ላይ ሠላም ሰፍኗል ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን የሰፈነ ሰላም ማጽናት የሑሉም ትኩረት ሆኖ በአንዳንድ የኪስ በታዎች ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን አይተናል ነው ያሉት።

ልማት ቀዳሚው አጀንዳ መሆኑን አይተናል ሲሉም ገልጸዋል።

በከተሞቹም ሆነ በገጠር ሕዝቡ ወደ ልማት ፊቱን አዙሯል ያሉት ሚኒስትሩ ከፈተና የተማረ፣ ወደ ድል የተሻገረ እድገት እና ብልጽግና መሻቱ የሆነ ቁርጠኝነት አይተናል፤ ይህንን ሁኔታ በማየቴ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትና የአካባቢው አሥተዳደር በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በፈጠሩት ችግር የቆሙ ፕሮጄክቶች በተደረጃ መንገድ ሥራ እንዲጀምሩ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የተጀመረው እና በፀጥታ ችግር የቆመው ቡሬን ከነቀምት የሚያገናኘው መንገድ እየተፈጠነ መሆኑንም ጠቁመዋል። በተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክም እየተፋጠነ ነው ብለዋል። ይህ በነቀምት የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ አራቱንም ወለጋዎች ይዞ የመውጣት አቅም ያለው መሆኑን አውስተዋል።

በነቀምቴ ከተማ ግሩም የኮርደር ልማት ሥራዎች ተጀምሯል ያሉት ሚኒስትሩ በምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች የተጀመረው የበጋ መስኖ በተለይም የስንዴ ልማት ሥራ በእጅጉ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዋዩ ቱቃ ወረዳ ሚኛ ኩራ ቀበሌ በስድሳ ስድስት ሄክተር ላይ በበጋ መስኖ እየለማ ያለን የስንዴ ማሳ ተዛዋውረው መጎብኘታቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ከ228 ሺ ሄክተር ባላይ መሬት በስንዴ ዘር እንደተሸፈነ ተረድተናል ነው ያሉት። የአርሶ አደሩን ምርቶች በተለይም የበቆሎ ምርት ፕሮሰስ የሚያደርጉ በአርሶ አደሩ ማኅበራት የለሙ የኢንዱስትሪዎችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል። ለዚህ ትልቁ አብነት በድጋ ወረዳ እፋ ከተማ የበቆሎ ዱቄትና ቂንጨ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓት በወለጋ በቆሎ በአማካይ 2200 ብር በኩንታል እየተሸጠ ነውም ብለዋል ሚኒስትሩ። ወለጋ ከግብርና አኳያ ትልቅ እምቅ አቅም እንዳለው በመግለጽ ይህንን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ ለመጪው ክረምት ለአረንጓዴ ዐሻራ እየተዘጋጁ ያሉ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎችንም ጎብኝተዋል፡፡ የቡና፣ የሙዝና አቮካዳ ችግኝ ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል። ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ በመጠኑ ከፍተኛ ድርሻ ይዞ በማቅረብ ወለጋ ግምባር ቀዳም መሆኑን በመጥቀስ የቡና ምርት ጥራት መጠበቅ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ አውስተዋል።

‘ወለጋ መሬቱ ከላይ ቡና ከታች እንደ ወረቅ፣ ፕላቲንየም፣ ሊትየም፣ ከሳል ድንጋይ፣ ማርብል የመሳሰሉ የከበሩ ማዕድናት የሚገኙበት፣ በሰብልም ሆነ በእንሰሳት ምርት እጅግ ትልቅ አቅም ያለው አካባቢ ነው’ ሲሉም ገልጸዋል።

አሁን የተገኘውን ሰላም በማፅናት፣ የተፈጠረውን የልማት መነቃቃት በማጠናከር አካባቢውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ መውሰድ ይቻላል ብለዋል ሚኒስትሩ።

‘በግሌ በአካባቢው ያለው የልማትና የሕዝብ መነቃቃት ትልቅ ተስፋ አሳድሮብኛል’ ያሉት ሚኒስትሩ የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄ የመሠረተ ልማትና የአካባቢው እምቅ አቅም እንዲገለጥ፣ ልማት እንዲፋጠን፣ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን፣ ኅብረ ብሔራዊነት እንዲጠናከር መሆኑን ገልጸዋል። ‘ይህ ከፓርቲያችን ውሳኔ እና አቅጣጫ ጋር ያው እና አንድ ነው’ ሲሉም አስፍረዋል።

‘የብልጽግና ፓርቲ በጉባዔ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎችን ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሰራን እስካሁን ከጉባዔ እስከ ጉባዔ በተገኙ ስኬቶች ላይ እየደመርን ከተጓዝን ያለምነውም እናሳካለን’ ሲሉም ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review