የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ ያደረገው መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በቀን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል ይላል፡፡ በተለይም ሴክተሩ በጊዜ ሂደት የወለደውና አዲስ ጽንሰ ሀሳብ የሆነው በምኅፃረ ቃል ማይስ (Meeting Incentives & Conference Exhibition) በሚል የሚታወቀው ዘርፍ ላይ ሀገራት አተኩረው በመስራት የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን እያሳደጉበት ስለመሆኑ መረጃው ያሳያል፡፡
የዓለም የጉዞ እና ቱሪዝም ካውንስል (WTTC) መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ የኮንፈረንስ ቱሪዝሙ ዋነኛ መሳሪያ ሆነው እያገለገሉ ያሉት የኮንቬንሽንና የኤግዚቢሽን ማዕከላት ናቸው፡፡ ዘርፉም ዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱንና በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሀገር ውስጥ ምርት አሰተዋጽኦ ሲኖረው ለ26 ሚሊዮን ሰዎችም የስራ እድል እየፈጠረ ስለመሆኑ መረጃው ይጠቁማል፡፡
ዓለም አቀፋዊ ከሆኑ ስብሰባዎች ጋር ተጣምሮ በሚካሄደው በዚህ የቱሪዝም ዘርፍ በአፍሪካ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ ያሉ ሀገራት ቀዳሚ ተጠቃሚ ሀገራት ናቸው፡፡ በተለይም የኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን ማዕከላት ግንባታ ንድፈ ሀሳብን ወደመሬት ለማውረድ የሚያግዙ የኮንቬንሽን ማዕከላትን በማዘጋጀት ከጥቅሙ ተቋዳሽ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ሀገራቱ በኮንቬንሽን ማዕከላቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከላት፣ በዘርፉ የተሰማሩ ጠንካራ ዓውደ መድረክ አዘጋጆችና ጠንካራ የጉዞ ወኪሎች በማዘጋጀታቸው የበለጠ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ይገለጻል፡፡
እንደ የአፍሪካ ኤግዚቢሽን አዘጋጆች ማኅበር አስተያየት ከሆነም የኮንቬንሽን ማዕከላት የአፍሪካን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ እና ዘላቂና የበለጸገ የከተማ ሥነ ምህዳርን ለመፍጠር የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የዓለም ከተሞች ቀን በግብጽ አሌክሳንድሪያ በተከበረበት ወቅት የዓለም አቀፍ ኮንግረስ እና ኮንቬንሽን ማህበር (ICCA) ሊቀመንበር ጋሪ ኮሪን እንዳሉት፣ የስብሰባ ማዕከላት ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት ወሳኝ አካል ናቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ ኬፕ ታውን፣ ጆሃንስበርግ፣ ኪጋሊ እና ናይሮቢ ያሉ ከተሞች የስብሰባ ተቋሞቻቸውን በብቃት በመጠቀም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በመሳብ በሚሊዮኖች ገቢ እያገኙበት ስለመሆኑ በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም የኮንቬንሽን ማዕከላት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸውና የዓለም ባንክን ዋቢ አድርገው ሲያስረዱ ባለሀብቶች የንግድ ሀሳባቸውን መሬት ለማውረድ የኮንቬንሽን ማዕከላትን በውስጣቸው የያዙ ከተሞችን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ጭምር ተናግረዋል፡፡
በእርግጥም እሳቸው እንደሚሉት የኮንቬንሽን ማዕከላት ይህን ያህል ተጽዕኗቸው የጎላ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እናገኝ ዘንድ የተወሰኑ የአፍሪካ ከተሞች ላይ ቅኝት ማድረጉ ተገቢነት ይኖረዋልና ወደዚያው እናምራ፡፡ የቅድሚያ ማረፊያችንን ደግሞ የሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ እናድርግ፡፡ በአፍሪካ እ.ኤ.አ እስከ 2014 ድረስ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ረገድ እምብዛም ሳትሰራ የቆየችው ሩዋንዳ አሁን ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የሙያ ማህበራትን ኮንፈረንስ በማስተናገድ ሁለተኛዋ ሀገር ለመሆን ችላለች። በ13 ነጥብ 6 ሄክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈው የኪጋሊ ኮንቬንሽን ማዕከል የተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በተከታታይ እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ኮንቬንሽን ማዕከሉ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ5 ሺህ በላይ ተወካዮችን ማስተናገድ የሚችሉ 18 የተለያዩ አዳራሾችን በውስጡ ይዟል፡፡ እንደዚሁም 292 ክፍሎች ያሉት ባለ 5 ኮከብ ሆቴል፣ 2 ሺህ 600 መቀመጫ ያለው የኮንፈረንስ ማዕከል እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ በውስጡ ስለመያዙ ከማዕከሉ ገፀ ድር ላይ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ተጀምሮ በ2016 የተጠናቀቀው ይህ ኮንቬንሽን ማዕከል ለግንባታው 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
የኪጋሊ ኮንቬንሽን ማዕከል ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺህ 322 በላይ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን አስተናግዷል፡፡ ለአብነትም በ2022 የኮመንዌልዝ የመሪዎች ስብሰባ፣ በ2016 የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም፣ 2017 ለአፍሪካ በየአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባዎች የተከናወኑት በዚሁ ማዕከል ነበር፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ ኮንግረስ እና ኮንቬንሽን ማህበር መረጃ ማዕከሉ ሩዋንዳ በአህጉሪቱ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ሁነቶች መዳረሻ እንድትሆን አሰችሏታል።

ሩዋንዳ በየዓመቱ እስከ 2 ሚሊዮን ቱሪስቶችን ተቀብላ የምታስተናግድ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ሰው ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ብቻ እግሩ ሩዋንዳን ይረግጣል፡፡ ለመዝናናት ከሚመጡ ቱሪስቶች ይልቅ ለኮንፈረንስ ብሎ ወደ ሩዋንዳ የሚመጣው ጎብኚ ለበርካታ ቀናት እንደሚቆይ ነው፡፡ ሩዋንዳ በማይስ ሴክተር ብቻ በየዓመቱ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የምታስገባ ሲሆን ይህም ማለት የቱሪዝም ሴክተሩ ከሚያመነጨው እስከ 20 በመቶ የሚሆነው እንደማለት ነው፡፡ የሩዋንዳ መስተንግዶ ዘርፍን ከማሳደግ ባለፈ ኪጋሊ በአፍሪካ ቀዳሚ የኮንፈረንስ መዳረሻ እንድትሆን የኪጋሊ ኮንቬንሽን ማዕከል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ከሁለት ዓመት በፊት በወጣ መረጃ ሩዋንዳ የስብሰባ፣ ኮንፈረንሶች እና ዝግጅቶች ዘርፍ አስደናቂ እድገት ያስመዘገበች ሲሆን ከ150 በላይ ጉባኤዎችን ባስተናገደችበት በዚሁ ዓመት ብቻ ከ91 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች ይላል ከሀገሪቱ ቱሪዝም መስሪያ ቤት የተገኘው መረጃ። በሩዋንዳ ኮንቬንሽን ቢሮ የማስታወቂያ ባለስልጣን ፍራንክ ሙራንጉዋ በኮንፈረንስ መገልገያዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን ጨምሮ የሀገሪቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይላሉ፡፡
ወደ ጎረቤት ሀገር ኬኒያ ናይሮቢ ስናቀና ደግሞ የኬንያታ ኢንተርናሽናል ኮንፈረንስ ማዕከልን እናገኛለን፡፡ የኬንያታ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል (ኪ.አይ.ሲ.ሲ) ሊቀመንበር የሆኑት ኢሩንጉ ኒያኬራ ስለ ተቋሙ ሲናገሩ ለዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ቀዳሚ መዳረሻ ለማድረግ የለውጥ ጉዞ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። በስብሰባዎች፣ ኮንፈረንሶች እና ኤግዚቢሽኖች ውስጥ የኪ.አይ.ሲ.ሲ ድርሻ ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ ስለመመጣቱም ይናገራሉ፡፡
ኬንያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም በምታገኘው ገቢ ተጠቃሚ ለመሆን የቻለች ሲሆን፣ በዘርፉ በምታደርገው እንቅስቃሴ ሳቢያም በርካታ ኮንፈረንሶች በሀገሪቱ እንዲካሄድ የተመቸች ሆና መገኘቷም ለምታገኘው ከፍተኛ ገቢ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል፡፡ ኬንያ ከቱሪዝም ዘርፍ በየዓመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት ትጠቀሳለች፡፡
የማዕከሉን አቅም በማሳደግ እና መጠነ ሰፊ የንግድ ስብሰባዎችን በማስተናገድ በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገበ ካለው የማይስ አገልግሎት ለመጠቀም ታቅዶ እየተሰራ ስለመሆኑ ሊቀመንበሩ ያስረዳሉ። እንደ ሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ አፈጻጸም ሪፖርት መረጃ በ2023 ከኬንያ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መካከል ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የመጡት 24 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የንግድ ዝግጅቶች እና ኮንፈረንሶች ፍላጎት በመጠቀምም የኮንቬንሽን ማዕከሉ ለኬንያ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አበርክቶው ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በእርግጥ ኬንያ ቀድሞውንም በዓለም ዙሪያ ቱሪስቶችን በመሳብ በተፈጥሯዊ ውበቷ እና በበለጸጉ ባህላዊ ቅርሶች ትታወቃለች። በተለይም የኬንያ ባህላዊ የቱሪዝም መስህቦች የሆኑት እንደ ታዋቂ የባህር ዳርቻዎቿ እና ልዩ ልዩ የዱር አራዊት ለዚህም በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን በማይስ ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ መዳረሻ ሀገር ለመሆን ከዚህም በላይ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ጠንካራ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ማሟላት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከ20 ዓመታት በፊት በሩን የከፈተው የኬፕ ታውን ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል ባስተናገደው ልዩ ልዩ የንግድና የመዝናኛ ዝግጅቶች አፍሪካን ከዓለም ጋር በማገናኘት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይባልለታል። የኬፕ ታውን ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል በአፍሪካ ውስጥ ለኮንፈረንስ፣ ለኤግዚቢሽኖች እና ለቢዝነስ ዝግጅቶች ተመራጭ መዳረሻ ነው። በየዓመቱ በአማካኝ እስከ 600 የሚደርሱ ዝግጅቶችን የሚያስተናግደው የኮንቬንሽን ማዕከሉ እ.ኤ.አ የ2010 የፊፋ የዓለም ዋንጫ እጣ አወጣጥ ስነ ስርዓትንም ያስተናገደ ማዕከል ነው፡፡
የኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ ከ3 ዓመት በፊት የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አስመልክቶ ባወጣው ጥናት የኬፕ ታውን ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል ለሀገሪቱ ጥቅል ምርት ላይ 53 ነጥብ 2 ቢሊዮን የደቡብ አፍሪካ ራንድ እንዳዋጣ አስፍሯል። እንደዚሁም ማዕከሉ በከተማው የከተማ መልሶ የማልማት ጥረት ውስጥ ትልቅ ሚና ከመጫወቱም በላይ ኢንቨስትመንት እና ልማትን መሳብ አስችሏል ይላል፡፡ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው የስርዓት ደረጃዎች መካከል የአይሶ 9001 (ጥራት ማኔጅመንት)፣ የአይሶ 14001 (የአካባቢ አስተዳደር) እና ኦሀሰስ 18001 (የስራ ጤና እና ደህንነት) ሰርተፊኬቶችን በአንድ ጊዜ በማግኘት በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮንቬንሽን ማዕከል ነው።
በጥቅሉ የኬፕ ታውንና ሌሎቹም ከላይ የጠቀስናቸው የኮንቬንሽን ማዕከላት የየሀገራቱን ኢኮኖሚ ከማጠናከር በተጨማሪ የፈጠራና ትምህርት፣ የግንኙነትና የበጎ አድራጎት ስራዎች መከወኛ እና የባህል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማበረታታት አጋዥ ስለመሆናቸው ተረጋግጧል።
በሳህሉ ብርሃኑ