የኮሚሽኑ ያለፉት ዓመታት ጉዞና የቤት ስራዎች

You are currently viewing የኮሚሽኑ ያለፉት ዓመታት ጉዞና የቤት ስራዎች

•  አጀንዳዎች ይፋ ተደርገው በእነዚያ ላይ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እንደሚከናወን ተጠቁሟል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመው በሀገሪቱ የአለመግባባትና የግጭት ምክንያት የሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ በመለየት፣ በተለዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ተቋቁሞ፣ ኮሚሽነሮቹ ከተሰየሙ በኋላ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ባለፉት ሶሰት ዓመታት በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ለማሳተፍ፣ ህብረተሰቡን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን ልየታ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተከናውኗል፡፡ በመቀጠልም ከተሳታፊዎች የአጀንዳ ሀሳብ የሚሰጡትን በመለየት አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር ከአማራና ትግራይ ክልሎች፣ በፌዴራልና ዳያስፖራ ደረጃ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ተካሂዷል፡፡

ምን ውጤት ተገኘ?

ሀገራዊ ምክክር በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚያስገኛቸው ውጤቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ባለፉት ሶሰት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች መልካም የሚባሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ያነሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ዛሬ ድንገት ብቅ ያሉ ሳይሆን ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የልዩነት ምክንያት የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የጋራ አጀንዳ በመቅረፅ በምክክር መፍታት እንደሚቻል እንደ ሀገር ግንዛቤ መያዙ እንደ ጥሩ ጅምርና ውጤት መታየት የሚችል ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን “ሁሉም አካል ችግሮቻችን በምክክር መፍታት ይቻላል” የሚል እምነትና አቋም አለው ማለት አይደለም። የማይካደው ከትናንት በተሻለ ዛሬ ላይ በመንግስት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለያዩ ማህበራትና እንደ ህዝብም መመካከር እንደሚያስፈልግ መግባባትና ግንዛቤ እየተያዘበት መጥቷል፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ሀይለማርያም ይህን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ መምህሩ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሀገራችን ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ መሰረታዊ ችግሮች መነሻቸው ምንድን ነው? የሚለው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መለየት መቻሉ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከአማራና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በበርካታ አካባቢዎች  በመንቀሳቀስ አጀንዳዎችን አሰባስቧል፡፡ ኮሚሽነሮችም በተቻለ መጠን ገለልተኛ በመሆን ስራዎችን ሲያከናውኑ ነበር፡፡ በተቻለ መጠን የሁሉንም ሀሳቦች ለማካተት የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው ውጤት ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ በመለየት ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ የሚያስተባብርና የሚያመቻች፣ በአንጻራዊነት ገለልተኛና ነፃ የሆነ ተቋም ተፈጥሮ መስራት እንደሚቻል በተግባር መታየቱ ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በየጊዜው አቅሙን በማሳደግ፣ ምክክር ካካሄዱ ብዙ ሀገራት በተለየ መልኩ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነትና አቅም፣ “ችግራችንን ራሳችን ለይተን፣ ራሳችን ተሳትፈንበት፣ መግባባት ላይ እንደርሳለን” በሚል ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት መስራቱ ትልቅ ለውጥ መሆኑን አቶ ጥበቡ ይገልጻሉ፡፡

ተሳታፊዎችን በመለየትና አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት ለሀገር የሚጠቅሙ ብዙ ልምዶች ተገኝተዋል፡፡ ተሳታፊዎችን ከበርካታ የህብረተሰብ ክፍል አሳታፊና ግልፅነት በተሞላበት መንገድ የተለዩበት ሂደት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ልምድ ከተገኘባቸው መካከል አንዱ ነው። በአጀንዳ አሰባሰቡም በመደማመጥ፣ በአንድ መድረክ መተያየት የማይፈልጉ የተራራቀ ሀሳቦች ያላቸው ሰዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን በአንድ ጠረጴዛ ላይ ተመካክረው የጋራ አጀንዳዎችን ማምጣት ችለዋል። ይህም መድረኮች ከተፈጠሩ ላይግባቡ ይችላሉ ወይም ፅንፍና ፅንፍ የወጣ ሀሳብ እንዳላቸው የሚታሰቡ ወገኖች መነጋገርና መግባባት እንደሚችሉ ያሳያል፡፡ ይህንን ባህል በማድረግ ወደፊት የሚያጋጥሙ ልዩነቶችን በሃይል አማራጭ ሳይሆን ተቀራርቦ የመፍታት ልምዱ ጥሩ ጅምሩ ላይ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር የአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች በአማራና ትግራይ ክልሎች፣ በፌዴራል እንዲሁም በዳያስፖራ ደረጃ ካሉት በስተቀር በአብዛኛው መሰብሰባቸው በራሱ እንደ ትልቅ ውጤት የሚጠቀስ እንደሆነ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ጠቁመዋል፡፡

ፈተናዎቹ ምን ነበሩ?

ኮሚሽኑ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት በሚያደርገው ጥረት ከመንግስት ጀምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ አጋር አካላት ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከፍተኛ ተስፋ የጣሉበት ሂደት ነው። በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምክክሩን በማካሄድ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ያጋጠሙ ፈተናዎች በተሰጠው ጊዜ በተሟላ ሁኔታ ማጠናቀቅ እንዳይችል እንዳደረጉት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ያስረዳሉ፡፡

ኮሚሽኑ ስራውን ሲጀምር በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ ጦርነት ነበር፡፡ ጦርነቱ ከቆመ በኋላም የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭቶች ታይተዋል፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ ስራውን ማከናወን ፈተና ነበር። ለምሳሌ፡- ኮሚሽኑ ስራ ያልጀመረበት የትግራይ ክልልን መጥቀስ ይቻላል። በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች በመኖራቸው ተሳታፊዎችን በመለየት የአጀንዳ ሀሳብ ለመሰብሰብ ረዘም ያለ ጊዜ አስፈልጓል፡፡

ሌላው ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ አዲስ እንደመሆኑ መጀመሪያ አካባቢ የግንዛቤ እጥረቶች ይታዩ ነበር። በኮሚሽኑ ገለልተኝነትና ነፃነት ላይ ጥያቄዎችን የሚያነሱም አልጠፉም፡፡ አንዳንዶቹ ጉዳዩን በደንብ ካለመረዳት፣ ሌሎቹ ከሚገባው በላይ በመጠበቅ (ሁሉም ችግር በምክክሩ እንዲፈታ በመፈለግ) እንዲሁም የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የተዛባ መረጃ በማሰራጨት የምክክሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በዚህ ረገድ የግንዛቤ ስራዎችን በማከናወን ሀገርን ከግጭት አዙሪት ለማውጣት ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን መግባባት ለመፍጠር ብዙ እንደተሰራ ቃል አቀባዩ ያነሳሉ፡፡

ሌላው የምክክሩን ሂደት አሳታፊነትንና አካታችነትን መርህ በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሂደቱ እንዲሳተፉ ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸው እንዲሁም በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላትም በበቂ ሁኔታ መሳተፍ አለመቻላቸው አሳታፊነትና አካታችነቱ የተሟላ እንዳይሆን አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የኮሚሽኑን የሶስት ዓመት የስራ አፈፃፀም ከገመገመ በኋላ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ይችል ዘንድ ተጨማሪ የአንድ ዓመት የስራ ጊዜ ሰጥቶታል፡፡ በወቅቱም የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በርካታ አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን አድንቀዋል፡፡ በቀሪ ጊዜያት ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ “ወደ ሂደቱ ያልገቡ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአጀንዳ ሀሳብ እንዲያቀርቡ፤ ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ ሀይሎችም የሚሳተፉበት ዕድል ካለ አሁንም ጥረቶች ማድረግ ያስፈልጋል” የሚሉ ሀሳቦችን አንስተዋል፡፡

ቀሪ ስራዎች ምንድን ናቸው?

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት የሀገራዊ ምክክሩን ስራዎች ለማጠናቀቅ እቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ ይገኛል፡፡ አንደኛ በአማራና ትግራይ ክልሎች የአጀንዳ ሀሳብ የማሰባሰብ ስራ ይከናወናል፡፡ በአማራ ክልል ከሞላ ጎደል ከጥቂት ወረዳዎች በስተቀር ተሳታፊዎች ተለይተዋል፡፡ የአጀንዳ ሀሳብ የማሰባሰብ ስራ ከክልሉ መንግስትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ አመቺ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ይካሄዳል፡፡

በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ ባሉ ችግሮች ምክንያት ኮሚሽኑ ስራውን በተሟላ ሁኔታ መስራት እየቻለ አይደለም፡፡ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ በመንግስት በኩል ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በዳያስፖራው ማህበረሰብ የአጀንዳ ሀሳብ የማሰባሰብ ስራ በቅርቡ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ የተሰባሰቡትን አጀንዳዎች መልክ ማስያዝ ተጀምሯል፡፡ በመቀጠልም  አጀንዳዎች ይፋ ተደርገው በእነዚያ ላይ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ይከናወናል፡፡ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮችም ተግባራዊ እንዲሆኑ ምክረ ሀሳቦች ተዘጋጅተው ለሚመለከታቸው አካላት ይሰጣል፤ መተግበራቸውም ክትትል ይደረጋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በምክክሩ ሂደት ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች ወደ መድረኩ እንዲመጡ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ሲሉ አቶ ጥበቡ ጠቁመዋል፡፡

ለስኬታማነቱ ምን ይጠበቃል?

እንደ ሀገር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የተፈጠሩት በዋናነት በእኛ በኢትዮጵያውያን ነው፡፡ እነዚህን በሀሳብ ልዩነትና አለመግባባት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በመመካከር መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ህዝብ የመከረበትና የወሰነበት ጉዳይ ፍሬያማ ስለሚሆን ሀገራዊ ምክክሩን መደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ይናገራሉ። ስለ ሀገር ሰላምና እድገት ስናስብ ኃላፊነቱ የመንግስት ወይም የተወሰኑ አካላት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ህዝብ ከችግሩ ጋር የሚመጣጠን የመፍትሔ ሀሳብ እንዲመጣ በደንብ መስራት አለበት፡፡

በምክክሩ ሂደት የኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አንዳንድ አካላት እንዳሉ የጠቆሙት ኮሚሽነር ሙሉጌታ፣ እነዚህ አካላት ከሩቅ ሳይሆን ቀረብ ብለው የሚሰራውን ስራ ማየት፣ ጉድለቶች ካሉም በመጠቆምና አስተያየት በመስጠት እያስተካከሉ መሄድ የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ “የምንሰራው ስራ የሀገር ሉዓላዊነትንና የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚጠቅም ካልሆነ በታሪክም ተወቃሽ እንደሚያደርገን በማመን ነው” ሲሉ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡                                                                                                                                                ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብና ወጣት ሀይል፣ ለእርሻ የሚሆን ሰፊና ለም መሬትና በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች፣ የመለወጥና የማደግ እምቅ አቅምና ተስፋ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ ሁሉ እያላት የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በውይይትና ምክክር መፍታትን ባህል ባለማድረጎ በግጭት አዙሪት ውስጥ ስትማቅቅ ኖራለች፡፡ ሀገራዊ ምክክሩም በማያግባቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ለመድረስና ዘላቂነት ያለው ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማምጣት የሚያስችል ትልቅ መሳሪያ በመሆኑ የተፈጠረው እድል እንዳይባክን መጠቀም ይገባል እንላለን፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review