ህይወት አድን በጎነት

You are currently viewing ህይወት አድን በጎነት

•  በከተማዋ 830 በጎ ፈቃደኞች የትራፊክ እንቅስቃሴውን በማስተናበር እየተሳተፉ ይገኛሉ

የዝግጅት ክፍላችን ፒያሳ ጊዮርጊስ አደባባይ ፊት ለፊት ባደረገው ቅኝት ጠዋት ላይ አሽከርካሪዎችም ሆነ እግረኞች ወደሚሄዱበት ቦታ ለመድረስ ይጣደፋሉ።

በጎ ፈቃደኞች ደግሞ ያለእረፍት አንዴ ተሽከርካሪዎችን፤ ሌላ ጊዜ ህብረተሰቡን በተለይም አቅመ ደካሞችን ደግፈው ያሻግራሉ፤  የመልካምነት ተግባራቸውንም ይከውናሉ፡፡ ይህ አይነቱ የበጎነት ስራ መከናወን ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ለመሆኑ የአገልግሎቱን ፋይዳ ነዋሪዎች እንዴት ይገልፁታል? ስንል አስተያየታቸውን እንዲያጋሩን ጠየቅን፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ሰላም አለሙ፣ “በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የበጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች ያሻግሩናል፡፡ ለትራፊክ አደጋ እንዳንጋለጥ በተነሳሽት እያደረጉት ያለው ስራ የሚደነቅ ነው፡፡ መልካምነታቸው የሚበረታታ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል” ትላለች። ነዋሪዎች በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎችን መስማትና በእግረኛ ማቋረጫ (ዜብራ) መንገድ ብቻ በመሻገር የትራፊክ አደጋን መከላከል ይኖርብናል ስትልም ሃሳቧን አጋርታለች፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ግርማ ሲሳይ በበኩላቸው በእግረኛ ማቋረጫ መንገድ በምሻገርበት ወቅት ብዙ ጊዜ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪዎች ህብረተሰቡን በተለይ አቅመ ደካሞች እና ተማሪዎችን ሲያሻግሩ እመለከታለሁ፡፡ እኛን ያለምንም ክፍያ ስለሚያገለግሉን  ልናመሰግናቸው፤ ክብር ልንሰጣቸው ይገባልም ብለዋል፡፡

“ሁለት ጓደኞቼን በትራፊክ አደጋ ካጣሁ በኋላ ነበር ወደ ትራፊክ ማስተናበሩ ተግባር ለመግባት የተነሳሳሁት” የሚለው ደግሞ በአራዳ ክፍለ ከተማ በጎ ፈቃደኛ የትራፊክ አስተናባሪ የሆነው ወጣት ዮሀንስ ዳዊት ነው፡፡ እንደ ወጣቱ ገለጻ፣ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ ፈቃድ እግረኞችና መኪኖችን የማስተናበር ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡ የመኪና አደጋ እንዳይደርስበት የእግረኛ ማቋራጫ መንገድን ተጠቅመው እንዲያቋርጡ ያስተባብራል፡፡ የእግረኛ ማቋረጫ መንገድን የማይጠቀሙ ሲያጋጥሙት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን ያስተምራል፤ በራሪ ወረቀት በማዘጋጀት መረጃ የመስጠት ስራም እየሰራ ይገኛል፡፡

አልፎ አልፎ በእግረኛ ማቋረጫ ላይ ሰው ሲያሻግር ለማለፍ የሚቸኩሉ አሽከርካሪዎች ከማጋጠም ውጪ የማስተናበሩን ተግባር በጥሩ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝ የሚገልፀው ወጣት ዮሃንስ፣ ህብረተሰቡና አሽከርካሪዎች ከትራፊክ አደጋ ራሳቸውን በመጠበቅ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል በማለት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በዚህ ስፍራ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ያለበት አካባቢ በመሆኑ በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች ያለ እረፍት ህብረተሰቡ የእግረኛ ማቋረጫን ብቻ ተጠቅሞ እንዲሻገር ሲያስተባብሩ ተመልክተናል፤ ይህም የሚበረታታና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡

ሌላው ቅኝት ያደረግንበት የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ካለባቸው አካባቢዎች ከአራት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ እየተሰራ በሚገኘው መስመር አምስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘውን የትራፊክ ማስተናበር ነው፡፡ በዚህ ስፍራ የተማሪዎች መውጫ ከሰዓት በኋላ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ነበር በስፍራው የደረስነው፡፡ እንደቃኘነውም በቦታው ምንም ዓይነት የትራፊክ አስተናባሪ አልነበረም፡፡

የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሽመክት በየነ በወቅቱ በሰጡን አስተያየት፣ “በጎ ፈቃደኞች በከተማዋ በተለያየ ቦታ ሲያስተናብሩ እመለከታለሁ። በተለይ ህፃናትንና አዛውንቶችን ደግፈው በማሳለፍ እያደረጉት ያለው ስራ መልካምነታቸውን የገለጠ ነው” ብለዋል።

በዚህ ስፍራ ቀድሞ በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች የዜብራ መንገድ ላይ ህብረተሰቡን ሲያስተናብሩ መመልከታቸውን የጠቆሙት አቶ ሽመክት፣ የኮሪደር ልማት ስራ ከተጀመረ እምብዛም አላያቸውም፡፡ ሆኖም በስራው ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ ስለሚኖር፣ ህብረተሰቡም አቧራውን ለመሸሽ በሚል ወደ መሃል አስፋልት ጭምር ስለሚገባ ለትራፊክ አደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በቦታዎቹ አስተናባሪዎች የተጠናከረ የማስተናበር ስራ ቢሰሩ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ራሄል መንግስቱም የአቶ ሽመክትን ሃሳብ ትጋራለች፡፡ በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች በሌሎች ቦታዎች እንደሚያደርጉት ተግባር ሁሉ በዚህ አካባቢም በሚፈለገው ደረጃ ቢኖሩ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ያስችላል ብላለች፡፡

የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር የበጎ ፈቃደኞች የትራፊክ ማስተናበር   ተግባር ምን ይመስላል? ሲል የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ግንዛቤና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ኩማን አነጋግሯል፡፡

አቶ ብርሃኑ በማብራሪያቸው፤ በመዲናዋ የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የትራፊክ ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በቅንጅት በመሆን በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የመንገድ ላይ ማሻሻያ ስራዎች ለአብነት የፍጥነት መቀነሻ ጉብታዎች መስራት፣ የመንገድ ላይ የትራፊክ መብራት፣ የቀለም ቅቦች፣ የመንገድ ላይ አመላካቾች ተከላና ሌሎችም ተከናውነዋል፡፡ በተለይ የኮሪደር ልማት ተግባራዊ በሆነባቸው አካባቢዎች ሙሉ የመንገድ ላይ ምልክቶች እየተሟሉ ሲሆን እነዚህ ተግባራት ቀጣይነት አላቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የበጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ በዚህም በከተማዋ 830 በጎ ፈቃደኞች ሲኖሩ፤ በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት፣ ጠዋትና ማታ በተለይ የትራፊክና የእግረኛ እንቅስቃሴ መጨናነቅ ባለባቸው አካባቢዎች ለአብነት መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ፒያሳ፣ አውቶቢስ ተራ፣ ሰባተኛ፣ የባቡር መሻገሪያ ባሉባቸው አካባቢዎችና በከተማዋ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በተለዩ 89 ቦታዎች ተመድበው እያስተናበሩ ይገኛሉ፡፡ ህብረተሰቡ የትራፊክ ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ፣ የትራፊክ ፍሰቱን በማስተናበር አደጋ እንዳይከሰት በከፍተኛ ሁኔታ እያገዙ ነው፡፡ በጎ ፈቃደኞች በሚያስተናብሩበት ወቅት የደረሰ የሞትም ሆነ ከባድ የአካል ጉዳት የለም ብለዋል፡፡

አምስት ኪሎ ማሪያም አካባቢ አስተናባሪዎች የሌሉ በመሆኑ እግረኛውም መኪናውም በጥድፊያና እየተጋፉ ሲሻገሩ ተመልክተናል፡፡ በቦታው የነበው የትራፊክ መብራት ተነስቷል፡፡ የእግረኛ ማቋረጫ ዜብራም የለም፡፡ ከዚህ አንፃር የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በጎ ፈቃደኛ በአካባቢው የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ በዚህ ስፍራ በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች እንደወትሮው ለምን አልተገኙም? ስንል በባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባን ጠይቀናል፡፡ ዳይሬክተሯ በሰጡት ምላሽ፤ “የበጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተመደቡባቸው ቦታዎች እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎ የትራፊክ አደጋ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች፣ ትልልቅ ስብሰባዎች፣ ኩነቶች፣ የደም ልገሳና እና ሌሎች ጉዳዮች ሲኖሩ በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች ለተወሰነ ሰዓትና ቀን ከተመደቡበት ቦታ በመውሰድ እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡ አምስት ኪሎ አካባቢም ከዚህ ቀደም የነበሩ ቢሆንም ሰሞኑን ያልተገኙበት ምክንያት በኮሪደር ልማቱ የተሰራው የአራት ኪሎ ፕላዛ ከመሬት ስር የእግረኛ መንገድ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ህብረተሰቡ በዚህ ስፍራ በምን መልኩ መጠቀም እንዳለበት ግንዛቤ የመስጠት ስራ እንዲሰሩ በጎ ፈቃደኞቹ ወደዚህ ስፍራ በመምጣታቸው ምክንያት የተፈጠረ ክፍተት በመሆኑ በቅርቡ ወደ ስፍራው በመመለስ መደበኛ የበጎ ፈቃድ ማስተናበር ተግባራቸውን ይጀምራሉ” ብለዋል፡፡

የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል አራት ኪሎ ፕላዛ ከመሬት ስር የእግረኛ መንገድ የማስተናበር አገልግሎት በሚሰጥበት ስፍራ በመገኘት ባደረገው ቅኝት፤ አምስት ኪሎ የነበሩት በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች ወደዚህ ስፍራ መምጣታቸውን አረጋግጧል፤ ሲያስተናብሩም ተመልክቷል፡፡

ካነጋገርናቸው በጎ ፈቃደኛ አስተናባሪዎች መካከል ወጣት አሰፋ ተስፋው ከዚህ ቀደም ስድስት ኪሎ አካባቢ በጥዋት ፈረቃ አምስት ኪሎ ደግሞ በከሰሃት ፈረቃ የማስተናበር ስራውን በመደበኛነት ሲሰራ እንደነበር ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት አራት ኪሎ ፕላዛ ከመሬት ስር የእግረኛ መንገድ አገልግሎቱ አዲስ በመሆኑ ህብረተሰቡ በመሬት ስር ባለው የእግረኛ መተላለፊያ እንዲጠቀም ግንዛቤ የመስጠትና የማስተናበር ስራ እየሠራ መሆኑንና ወደዚህ ስፍራ ከመጣ አንድ ወር እንደሆነው ተናግሯል፡፡

“የትራሪክ አደጋን ለመቀነስ የሚሰራው ስራ በአንድ ተቋም በሚደረግ ጥረት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን የሁሉንም ዜጋ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ተቋሙ ስራዎችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ እየሠራና ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ መረጃን በመስጠት የማንቃት ስራ ከሰሩ፤ መንገድ ተጠቃሚ፤ አሽከርካሪውም ይሁን ህብረተሰቡ በያገባኛል ስሜት ህግና ስርዓት አክብረው ከተንቀሳቀሱና ህግ የሚጥሱትን፣ ደንብ የሚተላለፉትን የሚገፅስና ወደ ስርዓት የሚያስገባ ከሆነ አደጋውን በጋራ መቀነስ ይቻላል፡፡”  ሲሉም ሁሉም አካል ከባለስልጣኑ ጎን በመሆን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አቶ ብርሃኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review