እንደ መግቢያ
ለአፍታ እንኳን በማያንቀላፋ እንቅስቃሴ ውስጥ ትገኛለች፤ አዲስ አበባ፡፡ በታቀደ መልኩ እየተመራ ያለው የመዲናዋ የልማት እንቅስቃሴ ውጤታማነቱ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ “አዲስ አበባን እንደ ስሟ እናደርጋታለን” የሚለው ቃል በተግባር ስለመገለጡ የልማት ትሩፋቱ ማሳያ ነው፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘው የፕሮጀክቶች ግንባታ እንቅስቃሴ የመዲናዋን ለውጥ እንደማለዳ ጀምበር በሩቅ የሚታይ አድርጎታል፡፡ 24/7 (በቀን ሃያ አራት ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀናት) በሚባል ደረጃ እየተከናወነ የቀጠለው የፕሮጀክቶች ግንባታ፤ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ እና ለእንግዶቿ
ምቹ፣ ፅዱ፣ ማራኪ እና ተስማሚ የመሆኗን ርዕይ እውን በማድረግ ላይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፈጣን የለውጥ ጉዞ፤ የኢትዮጵያን ታላላቅ ከተሞች አንቅቷል፡፡ ከጎንደር እስከ ሐረር፣ ከጅማ እስከ ጂግጂጋ፣ ከሀዋሳ እስከ አሶሳ… የሚታየው የከተሞች የልማት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ በጎ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ከሰሞኑ የደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ (የኮሪደር ልማት) እና የኬንያዋ ናይሮቢ (የወንዝ ዳርቻ ልማት) ለከተማነታቸው መሻሻል ያሳዩት መነሳሳት ከዓለም አቀፏ ከተማ አዲስ አበባ ፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ በተቀዳ የተሞክሮ እርሾ የመነጨ ስለመሆኑ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንደበታቸው የመሰከሩት ሀቅ ነው፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ ለአገልግሎት የበቁ ፕሮጀክቶች በጨረፍታ
የአዲስ አበባ አሁናዊ የዕድገት እና የለውጥ ጉዞ በውጤት እየታጀበ እንዲፋጠን ካደረጉ ዘርፈ ብዙ የሥራ እንቅስቃሴዎች መካከል የፕሮጀክቶች ግንባታ ይጠቀሳል፡፡ ከላይ በመግቢያው ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከለውጡ በኋላ በነበሩት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ የፕሮጀክቶች ግንባታ ስለ አዲስ አበባ ዓለም እንዲመሰክር ያስገደደውን ውጤት እንድታመጣ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከተማዋ ሕዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ እና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ያላቸው የልማት ሥራዎች ማምረቻ አውድማ እየሆነች መጥታለች፡፡
ከተማዋ ደረጃቸው እና አገልግሎታቸው የተለያዩ፣ ቁጥራቸው የበዛ ፕሮጀክቶች ማዕከል ስለመሆኗ ለነዋሪው መንገር ቀባሪን እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡ የሆነው ሆኖ፤ የመዲናዋን የፕሮጀክቶች ግንባታ እንቅስቃሴ ስፋት እና ግዝፈት ለመረዳት በአንድ ዓመት ውስጥ (ከመጋቢት 2016 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 2017 ዓ.ም.) ያለውን አፈፃፀም የሚያሳዩ የተወሰኑ አሃዛዊ መረጃዎችን እንመልከት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ያቀረቡት ሪፖርት በመዲናዋ ያለው የፕሮጀክቶች ግንባታ አፈፃፀም ሁኔታ አበረታች መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከንቲባዋ በሪፖርታቸው እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ 217 ግንባታዎች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል፡- የልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ህንጻ፣ የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ምዕራፍ አንድ፣ የየካቲት 12 ሆስፒታል እድሳት፣ የሼድ ግንባታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የተለያዩ ስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡
የስድስት ወሩን አፈፃፀም መሰረት አድርገን ቀላል ሒሳባዊ ስሌት ብንሠራ፤ አዲስ አበባ በየዕለቱ በአማካኝ ከአንድ በላይ የልማት ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት የምታበቃ እንደሆነች እንረዳለን፡፡ ይህን ውጤታማ የልማት እንቅስቃሴን ባህል እያደረገች በመጣችው አዲስ አበባ መሰል የፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በየጊዜው ለአገልግሎት የበቁትም ከፍሬያቸው ማቋደሳቸውን ጀምረዋል፡፡ ለአገልግሎት ከበቁ አንድ ዓመት እና ከዚያ በታች ዕድሜ ያስቆጠሩት የልማት ፕሮጀክቶች መሰል ትሩፋታቸውን ወደ መስጠት የገቡት ሳይውሉ ሳያድሩ ነው፡፡
ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ ለአገልግሎት ከበቁ በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት በመጠናቸውም ሆነ በአገልግሎታቸው ላቅ ያለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ለአብነት ያክል፡- የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ፣ በ5 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ 920 መኪናዎች በላይ የማስተናገድ አቅም ያለው የካ 2 መኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ የአራት ኪሎ ታክሲ ተርሚናልና ፕላዛ፣ በቀን 30 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው የቦሌ አራብሳ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ፣ የከተማዋን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ እና ለማሻሻል ዓላማ ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ስማርት ተንቀሳቃሽነት 2025 (Addis Ababa City Smart Mobility 2025) እንደሚጠቀሱ ከአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ጨምሮ በርካታ ትሩፋቶች እንደሚያስገኙ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ደጋግመው ያረጋገጡት እውነታ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር 2020 “Smart city development through mega projects: The case of Songdo” በሚል ርዕስ ሊ ኤች (Lee.H.) እና ፓርክ ጄ (Park J.) በተባሉ ምሁራን በተሠራ ጥናት ውስጥ እንደተመላከተው በከተሞች ውስጥ የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፤ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ይፈጥራሉ፡፡ መሰረተ ልማትን ያሻሽላሉ፡፡ የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ እና ጥራት ያሳድጋሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያግዛሉ፡፡ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ የአደጋ ተጋላጭነትን ይቀንሳሉ፡፡ የስማርት ሲቲነትን ጉዞ ያፋጥናሉ፡፡ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ተደራሽነትን ያሳድጋሉ፡፡

በከተሞች የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስለሚኖራቸው ፋይዳ ከላይ በጥናት የተጠቆመውን ሃሳብ የሚያጠናክር ሙያዊ አስተያየት የሰጡት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይን እና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ናቸው። እንደሳቸው ገለፃ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ እና በመከናወን ላይ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት ደረጃ ከፍ ያደረጉ፣ የስማርት ሲቲ እና የአካታች ወይም ሁሉን አቀፍ (Inclusive) መርህን የተከተሉ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባን የከተማነት ደረጃ በተጨባጭ ሁኔታ ከለወጡ እና ካሳደጉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን ያነሱት ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፤ ይህ ፕሮጀክት ለከተማ ዕድገት ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የመንገድ መሰረተ ልማት ያሳደገ እና ያሻሻለ፣ መንገድን ተከትለው የሚዘረጉ ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች (የቴሌ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና ፍሳሽ…) በዘመናዊ ሁኔታ ያሳደገ፣ ነዋሪው ማህበረሰብ እና ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በቅርብ ርቀት የሚያገኙበትን ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ጤናው የተጠበቀ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች (የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የህፃናትና አዳጊ መጫዎቻዎች፣ የእግረኛ እና ሞተር አልባ ተሽከርካሪ መንገዶች፣ የወንዝ ዳርቻ የመሳሰሉ ልማቶች) እንዲስፋፉ ትኩረት መስጠቱ ከከተማዋ አልፎ ለሀገር የሚጠቅም ቀጣይነት ያለው ትሩፋት እንዲገኝ ያደርጋል፡፡
የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጨምሮ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ እና ለአገልግሎት እንዲበቁ የከተማ አስተዳደሩ ያሳየውን ቁርጠኝነት እና ውጤታማ የሥራ አፈፃፀም ያደነቁት ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ወደኋላ ሲጎትቱ የነበሩ ክፍተቶችን በሚገባ መመለስ የቻሉ መሆናቸውን አንስተዋል። ከኒዮርክ እና ከጄኔቭ ቀጥላ ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ለስብሰባ፣ ለኮንፈረንስ፣ ለጉባኤ፣ ለኤግዚቢሽን፣ ለባዛር እና ሌሎች ሁነቶች ማከናወኛ እንዲበቁ የከተማ አስተዳደሩ ያሳየውን ቁርጠኝነት እና ውጤታማ የሥራ አፈፃፀም ያደነቁት ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ወደኋላ ሲጎትቱ የነበሩ ክፍተቶችን በሚገባ መመለስ የቻሉ መሆናቸውን አንስተዋል። ከኒዮርክ እና ከጄኔቭ ቀጥላ ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ለስብሰባ፣ ለኮንፈረንስ፣ ለጉባኤ፣ ለኤግዚቢሽን፣ ለባዛር እና ሌሎች ሁነቶች ማከናወኛ የሚሆኑ ግዙፍ፣ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የሕንፃ መሰረተ ልማቶችን ገንብታ ለአገልግሎት ማብቃቷ በብዙ መልኩ ሊገለፅ የሚችልን ጠቀሜታ ያስገኛል፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች አዲስ አበባን ለመሰለ ዓለም አቀፋዊ ከተማ በቂ ስላልሆኑ፤ ሥራው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባው ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ያልተቋረጠ ትሩፋት የሚሰጡ፣ ነዋሪውን ያስቀደሙ፣ እንግዶችን ያከበሩ፣ ከተፈጥሮ ጋር የተወዳጁ፣ የገቢ ምንጭ የሆኑ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ እና የሥራ ባህልን ያሻሻሉ … ስለመሆናቸው በየዕለቱ ያለውን እንቅስቃሴ ተመልክቶ መረዳት ይቻላል። ይህንን እውነታ የበለጠ ለመገንዘብ ለአገልግሎት ከበቃ የዓድዋ ድል መታሰቢያን በማሳያነት እንመልከት።
ለሁለት አስርት ዓመታት ታጥሮ ያለአገልግሎት በከረመ መሬት ላይ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ያስገኛቸው እና እያስገኘ ያለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያለፈውን የባከነ ጊዜ የሚያስቆጩ፣ ለቀጣይ ሥራ አቅም የሚሆኑ ተሞክሮዎች የተገኙበት እንደሆነ የሚያስረዱት የዓድዋ ድል የመታሰቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግሩም ግርማ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለከተማዋ እና ለሀገር ጥቅም መስጠት የጀመረው ያለአገልግሎት የተቀመጠው መሬት ወደግንባታ መቀየር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክቱ፤ በግንባታ ሂደት ውስጥ ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የሥራ ባህልን አሻሽሏል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር አግዟል፡፡ ተመርቆ ለአገልግሎት ከበቃ በኋላም የሚሰጠው ጥቅም ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስገኘ ሲሆን፤ ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በአስራ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ 246 ሺህ የሚደርሱ የሀገር ውስጥ እና የውጪ አገር ጎብኚዎች በክፍያ የጎበኙት ሲሆን፤ ይህንን ጨምሮ ከሱቅ ኪራይ፣ ከአዳራሾች ኪራይ፣ ከመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት ክፍያ፣ ከዓውደ ርዕይ ማሳያ ቦታ ኪራይ እና ከመሳሰሉ አገልግሎቶች በአስራ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ 126 ሚሊዮን ብር ገቢ አስገኝቷል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ፕሮጀክትም ዘርፈ ብዙ ትሩፋትን እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡ በተለይ አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ከማለዳው እየታዩ ያሉ እንቅስቃሴዎች አመላካች ናቸው፡፡ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ማዕከሉ፤ በውስጡ እያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 ትላልቅ አዳራሾች፣ 8 አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ እስከ 1 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አልጋዎችን የያዙ 2 ሆቴሎች፣ ከቤት ውጪ እስከ 50 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የኤግዚቢሽን ስፍራዎች እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶችን አሟልቷል። ፕሮጀክቱ ለአገልግሎት መብቃቱ ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንፍረንስና ኤግዚቢሽን ተመራጭና ተወዳዳሪ ማዕከል እንድትሆን የሚያግዝ ስለመሆኑ ከንቲባ አዳነች በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከግለሰብ እስከ ሀገር፣ አለፍ ሲልም አህጉር አቀፍ ጠቀሜታዎችን የሚሰጡ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እያመረተች ያለችው አዲስ አበባ፤ ቁጥራቸው 13 የሚደርሱ ነባር ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለፍፃሜ ለማድረስ እና ለአገልግሎት ለማብቃት በተለመደው የሥራ ትጋት እየተከናወነ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የካቲት አጋማሽ ላይ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በሪፖርታቸው መግለፃቸው ይታወሳል። 13ቱ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ጥሩ በሚባል የግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ የትራንስፖርት ቢሮ ሕንፃ፣ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪያል ክላስተር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት አንስተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የከተማውንና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንደሚያቃልሉ ተስፋቸውን ገልፀው፤ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በአጠቃላይ የአዲስ አበባን የለውጥ ግስጋሴ በማፋጠን የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ያሉትን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በተጠናና በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል ይገባል፡፡ የተጠናቀቁ እና በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም የአዲስ አበባን የተምሳሌትነት ጉዞ በስኬታማነት የሚያስቀጥል መንገድ መያዙን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ በአዲስ ወደ ተግባር የሚቀየሩትም የትላንትን እና የዛሬን ውጤታማ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት በመያዝ በተሻለ አፈፃፀም የሚከወኑበት ዕድል ሰፊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እናም አዲስ አበባን እንደ ስሟ እና ኃላፊነቷ በሁሉም መመዘኛ ተምሳሌት ሆና እንድትገኝ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል እንላለን፡፡
በደረጀ ታደሰ