እየጎለበተ ያለው የከተሜነት ባህሪ

You are currently viewing እየጎለበተ ያለው የከተሜነት ባህሪ

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እንብርት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ለበርካታ አስርት ዓመታት  ከስምና ዝናዋ በታች ኖራለች ሊባል ይችላል። እንደ እድሜዋ ያልዘመነች እና ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆነች ከተማ እየተባለች ትተችም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን መልካም የለውጥ እንቅስቃሴዎች ይታዩባት ጀምሯል።  

ከተማዋ ስሟንና ደረጃዋን የምትመጥን እንድትሆን እየተከናወኑባት ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ነው። የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በስኬት ተጠናቅቆ ሁለተኛው ዙርም በመፋጠን ላይ ይገኛል። ይህም ከተማዋን ሳቢ፣ ለኑሮ የተመቸችና አዲስ ገፅታን የተላበሰች አድርጓታል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ሰፊ የእግረኛ፣ የተሽከርካሪና የብስክሌት መንገዶችት ማካተቱ፣ መልከ ብዙ የመዝናኛ ስፍራዎችን መፍጠሩ፣ የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማብዛቱ የምቾት ደረጃውን አሳድጎታል፡፡  የታክሲና የከተማ አውቶብስ ማቆያ፣ መጫናኛ ማውረጃዎችንም አዘምኗል።

የአዲስ አበባን ገጽታ አጉድፈው የነበሩ ስፍራዎች የኮሪደር ልማቱ እንደ አዲስ ተወልደዋል፤ ተውበዋል፡፡ በዚህም ከተማዋ እንደ ስሟ ውብ አበባ እየሆነች ነው ሊባል ይችላል፡፡ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ከመገናኛ እስከ አያት እና ከፒያሳ እስከ መስቀል አደባባይ ያለው መስመር እንዲሁም ሌሎች የኮሪደር ልማቱ የጎበኛቸው ስፍራዎች ለዚህ አበባል ምስክር ናቸው፡፡

እነዚህን የልማት ስራዎች ተከትሎ በከተማዋ አዳዲስ የስራ ባህሎች እየሰፈኑ ይገኛሉ። ለአብነትም የኮሪደር ልማቱ በተሰራባቸው መስመሮች የሚገኙ የንግድ ተቋማት እስከ ምሽት እንዲሰሩ ተደርጓል። የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካርዎችም የአገልግሎት ሰዓታቸውን አራዝመው እስከ ምሽት 4:00 እንዲሰሩ መመሪያ ተላልፏል። ለመሆኑ እነዚህ እርምጃዎች አዲስ አበባ የከተሜነት ባህሪን እንድትላበስ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ ከመደጎም አንጻር ምን አበርክቶ አላቸው? ስንል ምሁራንን ጠይቀናል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ማህበረሰቦች መኖሪያ፣ የዲፕሎማቲካ ማዕከል፣ አህጉራዊና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ የማታ ክፍለ ጊዜ አገልግሎትን ማስፋፋት የውዴት ግዴታ መሆኑን ምሁራኑ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይን እና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) አዲስ አበባ ካላት ዓለም አቀፍ ስምና ዝና አንጻር ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ስለሚኖሩባት ስልጣኔዋም በዚያው ልክ መሆን አለበት ብለዋል።

የመንገድ ዳር የንግድ ተቋማትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተጨማሪ ሰዓታትን እንዲያገለግሉ መደረጉ ከተማዋ ከደረሰችበት ዕድገት አንጻር ትክክለኛ እርምጃ ነው ሲሉም አክለዋል። አዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ይዞላት በመጣው በረከት እንደ ንስር እራሷን እያደሰች የውበት ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች፡፡ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የበርካቶችን ቀልብ ገዝታ የዓለም ታላላቅ ተቋማትን ጉባኤዎች ያስተናገደችው ይህች ከተማ አሁንም የበለጠ ለመድመቅ ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ምዕርፍ በማፋጠን ላይ ትገኛለች፡፡

ከዚህ በፊት ሰዎች ምቾት በሌለው መንገድ ይንቀሳቀሱ እንደነበር አውስተው፣ አሁን የመንገድ ዳርቻዎች በመዋባቸውና በመብራት በማሸብረቃቸው ሰላማዊና ምቾት ያለው ከባቢ ሆነዋል፡፡ የመንገድ ዳርቻዎች ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባቸውና አማራጭ የመዝናኛ ስፍራዎችም ለመሆን አብቅቷቸዋል። ይህም አዲስ አበባ እየዘመነችና የስራ ባህሏም ተቀይሮ የከተሜነት ባህሪን እያዳበረች ለመምጣቷ ማሳያ ነው የሚል ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

በኮሪደር ልማት ስራ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕንጻዎች እንዲታደሱ ተደርጓል፤ የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ መንገዶች እና እግረኛ መንገዶች ተገንብተዋል፤ የመንገድ ዳር መብራቶችም እየተተከሉ ነው፡፡ በጥቅሉ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ምቹ እያደረጋት ይገኛል፡፡ ይህም ምቹ የንግድ ስራ እና የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲፈጠር አድርጓል። ከዚሁ መነሻነት የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የሚገኙ የንግድ ተቋማትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ተሽከርካሪዎች እስከ ምሽት አራት ሰዓት እንዲሰሩ ተደርጓል። ይህም የከተሜነት ባህልን ከማዳበር እና የከተማዋን ገፅታ ከማጉላት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙም ከፍትኛ መሆኑን የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኙ አቶ ኪሩቤል ሰለሞን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ማህበረሰቦች መኖሪያ፣ የዲፕሎማቲካ ማዕከል፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ የማታ ክፍለ ጊዜ አገልግሎትን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ለከተማዋ ሁለንተናዊ  እድገት አበረታች ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ አቶ ኪሩቤል ገለጻ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ለከተማዋ እድገት ጥሩ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ይህን መስመር ተከትሎ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስከ ምሽት ሰዓት ድረስ አራዝመው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ ለአገልግሎት ሰጪዎች ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡

ከነበረው ሰዓት በላይ ሲሰራ ምርታማነት እና ትርፋማነት ይጨምራል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያ የስራ ሰዓት በተራዘመ ቁጥር የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ጉልህ ነው፡፡ በተለይ የስራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም የስራ ሰዓት ሲጨምር በሁለት ፈረቃ የመስራት ዕድል ስለሚፈጠር ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ስራ የማስገባትን አጋጣሚ ይሰጣል፡፡ በዚሁ ልክ ከተማዋ የምታገኘው ገቢም እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ከተማዋ ከሌሎች ዓለም ቀፋዊ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ለከተማዋ እድገት  እያደረገ ያለው ወጥነት ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ባለሙያው ጠቅሰው፣ አጋጣሚው ለነዋሪዎችም  ቀልጣፋ የትራንስፖርት እና የንግድ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የኮሪደር ልማትን ተከትሎ አገልግሎት የሚሰጡ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስከ ምሽት 3 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ ወስኗል፤ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም እስከ ምሽት 4 ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው መወሰኑ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከምሽቱ 4 ሰዓት በፊት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያቋርጡ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን መቅጣት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ይህን እንዲያደርግም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በደንብ ቁጥር 185/2017 የተደነገገው ደንብ እንደሚፈቅድለት መግለጹ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሠረት ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት በፊት የትራንስፖርት አገልግሎትን ማቋረጥ፣ ከስምሪት መስመር ውጪ አገልግሎት መስጠት፣ አቆራርጦ መጫንና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ካወጣው ህጋዊ ታሪፍ ውጪ ህብረተሰቡን ማስከፈል እንደማይቻል ቢሮው አሳስቧል፡፡

በደንቡ ላይ የተቀመጡትን ክልከላዎች ተግባራዊ በማያደርጉና ከቢሮው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ አሰራርና መመሪያ ውጪ በህገ ወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ላይ በደንቡ በተቀመጠው የቅጣት እርከን መነሻነት አምስት ሺህ ብር የሚቀጣ ይሆናል ተብሏል፡፡

ቢሮው አገልግሎት ሰጪዎች በአገልጋይነት ስሜት ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ቢሮው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ህብረተሰቡም አገልግሎቱን በሚያደናቅፉ ህገ-ወጥ አገልግሎት ሰጪዎች ሲያጋጥሙት በነፃ የስልክ መስመር 9417 ወይም በአካል በአቅራቢያዎ በሚገኝ የትራንስፖርት ቅርጫፍ ፅሕፈት ቤቶችና የትራንስፖርት ዘርፍ ባለሙያች የተሽከርካሪውን ሰሌዳና ሰዓት በመያዝ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ታድያ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰዓት እስከ ምሽት መራዘም የሰዎችን ዝውውር በማቀላጠፍ ለከተማዋ ተጨማሪ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ አውስትራሊያዊው ደራሲውና የከተማ ልማት ባለሙያው ጄ.ፒ. ጎድርድ የመንገድ ዳር የንግድ እንቅስቃሴዎችና የትራንስፖርት አቅርቦት መዘመን በከተሞች ዕድገት ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን “ሰብ ሰርፌስ ደቨሎፕመንት ኢን ዘ አርባን ኢንቫይሮንመንት” በተባለ ጥናታዊ ፅሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ በዓለም ላይ እንደ ሆንግ ኮንግ፣ ማድሪድና የቻይናዋ ጓንግዙ ከተሞች በዚህ ረገድ በትልቁ ስለመስራታቸው አውስተዋል።ይህም አዲስ አበባ ዘግይታም ቢሆን የጀመረቻቸው መሠል ተግባራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡

በከተማ የሚሰሩ የውስጥ ለውስጥ መዝናኛዎች የተለመዱና ለከተሜነት መለያ መሆናቸውንም በመጥቀስ ይህም፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ይዘረዝራል። በተለይም የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ የበለጠ ንጹህ እና ለአካባቢ ተስማሚና ምቹ የቦታ አጠቃቀምን ለመፍጠር፣ ለእግረኞች ደህንነቱ የተጠበቀ መሸጋገሪያ ለመፍጠር አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ይላል፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2030 በዓለም ላይ በከተማ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር ወደ 61 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል በጥናታዊ ፅሑፉ ተገልጿል፡፡ ይህም የከተማ ቦታዎችን ለተለያዩ ተግባራት አብቃቅቶ መመደብና መጠቀም ግድ የሚልበት ወቅት መደረሱን አመላካች ነው፡፡ በከተሞች የሚሰሩ ፕላዛዎች የንግድ ስርዓትን ከማዘመንና የከተሜነት መንፈስን ከመከሰት ባሻገር ጎብኝዎችን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ያደርጋሉም ይላል፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review