

ከተሞች ለነዋሪዎችና ቱሪስቶች ከሚያቀርቧቸው ቁልፍ አገልግሎቶች መካከል ትራንስፖርት ተጠቃሽ ነው፡፡ ዘመናዊና ምቹ ከተሞች ለዜጎቻቸውና ጎብኚዎች አስተማማኝ፣ ፈጣን፣ ተደራሽ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡
አዲስ አበባ ከተማም ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹና አካባቢያዊ ተስማሚነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተጋች ትገኛለች። በከተማዋ በትራንስፖርት ዘርፍ በትኩረት እየተሰራባቸው ከሚገኙ መሰረተ ልማቶች መካከል የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ይጠቀሳል፡፡
ሰሞኑንም ዘመኑን በዋጁ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን ተደራሽ የማድረግ ጥረት አካል የሆነው የካ ሁለት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ግንባታው ተጠናቅቆ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተመርቆ ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡
የተሽከርካሪ ማቆሚያው ቅጥረ ግቢውን ጨምሮ 7 ሺህ 306 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አርፏል፡፡ ከመሬት በታች ሁለት፣ ከመሬት በላይ አምስት ወለሎች በድምሩ ስምንት ወለሎች አሉት፡፡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት፣ ሦስት የመኪና ማጠቢያ፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ ዘመናዊ መፀዳጃ ቤት፣ የተሽከርካሪና ሰው አሳንስር አገልግሎት፣ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የኦፕሬሽን ሲስተም ማዕከል ፣16 ሱቆች፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ፣ የማስታወቂያ አገልግሎትና ሌሎች የመኪና ተያያዥ አገልግሎቶችን አካቶ የተገነባ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ነው። በመንግስት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት በዓይነቱ በከተማዋ የመጀመሪያ የሆነ የህንፃ የመኪና ማቆሚያ እንደሆነ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ ዘመናዊና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ የመኪና ማቆሚያዎች መስፋፋት አዲስ አበባ ስማርት ሲቲ ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥናል፡፡ ከስማርት ሲቲ ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል ስልጡን እንቅስቃሴ (ስማርት ሞቢሊቲ) አንዱና መሰረታዊ ነው፡፡ ስማርት ወይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደግፈው አገልግሎት የሚሰጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የፓርኪንግ መሰረተ ልማቶች በኮሪደር ልማት፣ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎንና ራሱን ችሎ እየተገነባ ሲሆን፤ ይህም በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነስ እና የተሳለጠ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመፍጠር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የተነቃቃ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ዳንኤል (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ የፓርኪንግ ስፍራዎች ግንባታ በአዲስ አበባ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን (ማስተር ፕላን) የመሬት አጠቃቀም ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አኳያ ለመሰረተ ልማቱ ትኩረት መስጠቱ ጤናማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ይፈጥራል። ለሰዎች ንብረታቸው በአግባቡ እንዲጠበቅ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ትኩረት ያልተሰጠውና ክፍተት የሚታይበት አገልግሎት ነበር፡፡ መንገድ ዳርና ከመንገድ ውጪ ባሉ ቦታዎች በርካታ ተሽከርካሪዎች ፈሰው ይታያሉ፡፡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች አገልግሎቱ ስርዓት ወዳለውና ደረጃውን ወደጠበቀ አካሄድ እየሄደ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ቀደም ሲል መንገድ ለመንገድ ይቆም የነበረውን መኪና በስርዓት አንድ ቦታ ላይ እንዲቆም፣ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ አሁን ላይ የኮሪደር ልማት በተሰራባቸው መንገዶች በተፈቀደ ቦታ ካልሆነ በስተቀር መኪና ማቆም በመከልከሉ የትራፊክ ፍሰቱ ምን ያህል የተሳለጠ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ከዚህ አኳያ የመኪና ማቆሚያው የከተማዋን ዘላቂ ልማት የሚያግዝና ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የስማርት ሲቲ ዘርፍ ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፣ “ስማርት ሞቢሊቲ” ከትራንስፖርት ጋር የሚገናኝ ሲሆን፤ የምርት እንቅስቃሴ፣ መረጃ እና ሰዎችን የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም ከቦታ ወደ ቦታ ማጓጓዝ መቻል ጋር ይገናኛል፡፡ ቱሉ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የትራንስፖርት ስርዓቱን ማዘመን፣ የትራንስፖርት መሰረተ- ልማቱን መገንባትና በቴክኖሎጂ ታግዞ መጠቀም በብዙ መልኩ ኢኮኖሚውን ይደግፋል። የስማርት ፓርኪንግ ግንባታ (መስቀል አደባባይ፣ መገናኛ፣ የካ አካባቢ ያሉ የመኪና ማቆሚያዎች)፣መንገዶች ግንባታ እና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችና ስራዎች አዲስ አበባ ስማርት ሲቲ ለመሆን የያዘችውን ግብ ለማሳካት የሚያግዝ ነው።
“ከዚህ ቀደም በአጋጣሚ እንጂ ታቅዶ ለመኪና ማቆሚያ ትኩረት ተሰጥቶ አይሰራም ነበር፡፡” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በመንግስት የተገነቡ የፓርኪንግ ቦታዎች ብዛት ሁለት ሲሆኑ ከ500 በላይ መኪናዎችን የማቆም አቅም ያልነበራቸው ናቸው፡፡ እንዲሁም አንድ ተርሚናል ብቻ ነበር ያለው፡፡ ከለውጡ በኃላ በተሰራው ስራ 150 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች የተገነቡ ሲሆን፤ የካ ሁለትን ጨምሮ 35 ሺህ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችሉ እንዲሁም 49 የሚደርሱ ተርሚናሎችን በመገንባት የትራንስፖርት ስርዓቱን ለማዘመን እየተሰራ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ገልፀዋል፡፡
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች እንደገለፁት፣ የመኪና ማቆሚያው በተለወጠ አስተሳሰብ የተሰራና የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚያዘምን ትልቅ ትርጉም ያለው መሰረተ ልማት ነው፡፡ መሰረተ ልማቱ በሾላና መገናኛ መካከል ባለው ስትራቴጂክ ቦታ የተገነባ ነው፡፡ ሾላ አካባቢ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ያለበት፣ ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅና መኪና ለማቆም የሚያስችል ስፍራ እጥረት ያለበት እንደነበር ያነሱት ከንቲባዋ፤ የመኪና ማቆሚያው መገንባት የንግድና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በከተማዋ የፓርኪንግና የተርሚናል አገልግሎት በሰፊው ሲገነባ ዓላማው የትራንስፖርት አገልግሎቱን ምቹና የተሳለጠ እንዲሆን ማድረግ ነው። አገልግሎቶችን የማሳለጥ ጥረትም የህዝብን የኑሮ ጫና የመቀነስ አካል ነው፡፡ የመኪና ማቆሚያው ተገልጋዮች ከዝናብና ፀሐይ ተጠብቀው ምቾትና ክብር በጠበቀ መልኩ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉና ከተማዋን የማዘመን ጥረት አካል እንደሆኑ ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ የመኪና ማቆሚያው በተመረቀበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የከተማ አስተዳደሩ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት ብቻ ሳይሆን የመጪውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ስራ እያከናወነ ነው፡፡ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአንደኛውና ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የተሽከርካሪ፣ የእግረኛ፣ የብስክሌት፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የህዝብ ትራንስፖርት ተርሚናል፣ የአውቶብስና የታክሲ መጫኛና ማውረጃ መሰረተ ልማቶች በስፋት ተሰርተዋል፤ በመሰራት ላይም ናቸው፡፡ ለአብነትም የመስቀል አደባባይ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአንድነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የታላቁ ቤተ መንግስት የመኪና ማቆሚያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኤልያስ ዘርጋ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደገለፁት፣ የመኪና ማቆሚያዎች መስፋፋት የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥና የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ብዙዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ መንገዶች ባለ ሁለት መስመር ናቸው፡፡ የተሻለ የሚባሉት ደግሞ ባለሶስት መስመር ያላቸው ናቸው፡፡ ባለሶስት መስመር መንገድ ከሆነ አንደኛው ለተሽከርካሪ ማቆሚያ የሚውልበት፣ አንደኛው በግራ በኩል ለሚታጠፉት አገልግሎት ስለሚሰጥ በአግባቡ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የመሀሉ ብቻ ነው፡፡
የፓርኪንግ መሰረተ ልማቶች በስፋት ተገንብተው ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ እንዳይቆሙ ከተደረገ፣ ሦስቱም መስመሮች ወይም ሁለቱ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ በመፍጠር የትራፊክ ፍሰት ስርዓቱን ያሻሽላል፡፡ ሰዎች መንገድ ዳር ላይ መኪና ለማቆም ሲሞክሩ ከፊት አሊያም ከኋላ ያለን ተሽከርካሪ ፍሬቻ ወይም መብራት የሚገጩበት፣ እግረኞች ላይም አደጋ የሚያጋጥምበት አጋጣሚ እንደነበርና የመኪና ማቆሚያው ይህንን በመቅረፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ኢንጂነር ኤልያስ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተገነቡ ያሉ የመኪና ማቆሚያ መሰረተ ልማቶች ወደፊት የሚፈጠረውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ በቋሚነት አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡
ከቦታ አጠቃቀም አኳያም ለምሳሌ የካ ቁጥር ሁለት የመኪና ማቆሚያ የህንፃ ሳይሆን የመሬት ላይ መኪና ማቆሚያ ቢሆን 125 ተሽከርካሪ ብቻ ነበር የሚይዘው፡፡ በቋሚነት አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል መልኩ በመገንባቱ ግን አቅሙ በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ መኪናዎችን ወደ ማስተናገድ አድጓል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሁሉም ረገድ ዕድገት እያሳየች ትገኛለች። የህዝብ ቁጥሯ፣ የተሽከርካሪዎች እና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ መጥተዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ በአዲስ አበባ ከተማ ተመዝግበው የሚገኙ ናቸው፡፡ ከተማዋ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል በመሆኗ ከሁሉም ክልሎች ተሽከርካሪዎች ይገባሉ፤ ይወጣሉ፡፡ በዚህም የተነሳ የተሽከርካሪው ቁጥርና የትራፊክ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የነበራት የመኪና ማቆሚያ መሰረተ ልማቶች ያሉትን ተሽከርካሪዎች በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻላቸውና የአጠቃቀም ክፍተቶች በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ላይ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህም ሳይሰራ የቆየውን ይህንን ውዝፍ የቤት ስራ ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚሰኝ ነው እንላለን፡፡
በስንታየሁ ምትኩ