
ከሚሰራበት ተቋም በእህቱ ስም ከአንድ መቶ ሺ ብር በላይ ያጭበረበረን ሙያተኛ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ(ኤ ኤም ኤን) ሚያዚያ 6/2015 ዓም
ከሚሰራበት ተቋም በእህቱ ስም ከአንድ መቶ ሺ ብር በላይ ያጭበረበረን ሙያተኛ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ተቋማት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡
ተጠርጣሪው ግለሰብ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወሎ ሰፈር ከሚገኘው ሸዋ ሾፒንግ ሴንተር ውስጥ የሂሳብ ባለሙያ ሲሆን እህቱን በድርጅቱ ውስጥ ሰራተኛ ሳትሆን የድርጅቱ ሰራተኛ በማስመሰል በወር የ9ሺ 8 መቶ ብር ደመወዝተኛ በማድረግ በሱፐር ማርኬቱ ስር ከሚገኙ 12 ቅርንጫፎች በእህቱ ስም በአዋሽ ባንክ በተለያዩ ቅርንጫፎች 1መቶ 17ሺ 6መቶ ብር ገቢ እንዲሆንላት ያደርጋል፡፡
ድርጅቱ ከባንኩ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ጉዳዩን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለላንቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት አድርጎ ግለሰቡ ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡
እህቱ በተጭበረበረ መንገድ ገቢ ከተደረገላት ገንዘብ ውስጥ ለግለሰቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ ያደረገችለት 68 ሺ ብር ማስመለስ ተችሏል፡፡
ማንኛውም ግለሰብ ወደ ባንክ ሂሳቡ ብር ገቢ ሲደረግለት የገንዘቡን ምንጭና የላከለትን ግለሰብ የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደለበት እና ተቋማትም ተገቢውን ቁጥጥር ሊያሰርጉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።