
የህይወት መሰዋዕትነት ለሚከፍለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኤ ኤም ኤን) ግንቦት 20/2015 ዓ.ም
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር በኮየ ፈጬ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ነዋሪዎች “መከላከያ ሰራዊታችን አንድነታችንን ይገነባል” የሚሉና ሌሎች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፉ የተለያዩ መፈክሮች በመያዝ ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም መከላከያ ለሀገር ዘብ በመቆም የህይወት መሰዋዕትንት የሚከፍል መሆኑን ጠቅሰው ወደ ፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ፤የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጦርነትን በድል የሚያጠናቅቅ ብቻ ሳይሆን ሰላምን በማስጠበቅ አርዐያ ነው ብለዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሀገራችን ታሪክ ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሰላምን እንዴት ጠብቆ ማስተላለፍ እንደሚቻል አረጋግጧልም ነው ያሉት፡፡
ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላልን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ፤ ህዝቡ ለሰጠው ድጋፍና ላሳየው አጋርነት በሰራዊቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የህዝቡን ደጀንነትና አለኝታነትም ሰራዊቱ የጀመረውን ሀገርን የመጠበቅ ተልዕኮ በተሻለ ሞራልና ሃላፊነት ለመወጣት የሚያነሳሳው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ህገመንግስታዊ ሀገረ መንግስቱን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት ያሉት ሌተናል ጀኔራል ሹማ ከዚህ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው አሳስበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ከ12ቱም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ስራ ሃላፊዎችና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በረውዳ ሸምሱ