ሀምሳ አለቃ የወርቅ ውሀ ጌታቸው ለመከላከያ የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኘች

AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም

በናይጀሪያ አቡጃ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 2ተኛው የመላው አፍሪካ የጦር ሀይሎች ስፖርት ፌስቲቫል ኢትዮጵያን የወከለው የመቻል ስፓርት ክለብ አትሌቲክስ ቡድን በሀምሳ አለቃ የወርቅ ውሀ ጌታቸው የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል።

በናይጀሪያ አቡጃ ከተማ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 2ተኛው የመላው አፍሪካ የጦር ሀይሎች ስፖርት ፌስቲቫል መካሄዱን ቀጥሏል፡፡

በእለቱ ፍፃሜያቸውን ካገኙ ሦስት ውድድሮች አራት ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ እንደተቻለም ተገልጿል።

በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች በተካሄደው የፍፃሜ ውድድር ሀምሳ አለቃ የወርቅ ውሀ ጌታቸው አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ስትሆን ሀምሳ አለቃ አያልፍም ዳኛቸው የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችላለች።

በሌሎች የውድድር ዘርፎች በርዝመት ዝላይ ሴቶች ምክትል አስር አለቃ በፀሎት አለማየሁ የብር ሜዳሊያ ስታገኝ በሴቶች ዲስከስ ውርወራ አስር አለቃ ዙርጋ ኡስማን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

በውድድሩም ወቅት በናይጀሪያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ለገሰ ገረመውና ሌሎች ዲፕሎማቶች እና የስታፍ ሰራተኛች በውድድሩ ድጋፍ ሠጥተዋል።

እስካሁን ባለው ውድድር በአጠቃላይ የመቻል ስፖርት ክለብ 01 ወርቅ 04 ብር አጠቃላይ 05 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችለሏል።

በተመሳሳይ የ400 ሜትር ወንድና ሴት ማጣሪያ የተሳተፉት የመቻል አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ለፍፃሜ አልፈዋል።

የውድድሩ መርሀ ግብር የሚቀጥል ሲሆን በወንዶች የርዝመት ዝላይ፣ በወንድና ሴት ጦር ውርወራ፣ በወንድና ሴት 400 ሜትር እና በወንዶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ የፍፃሜ ውድድር እንደሚደረግ ከመከላከያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review