ሀገሪቱ በስፖርቱ ዘርፍ ያላትን አቅም ለመጠቀምና ለማሳደግ ይሰራል- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
AMN-ጥር 27/2017 ዓ.ም
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ከዛሬ ጀምሮ ለ10 ቀናት በወላይታ ሶዶ ይካሄዳል።
ውድድሩን በማስመልከት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።
“የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት፣ ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው በዚሁ የጎዳና ላይ እንቅስቃሴ የወላይታ ሶዶና አካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ባስተላለፉት መልዕክት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብቁ እና ንቁ ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ስፖርት ለአብሮነት፣ ለአንድነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለገጽታ ግንባታ ያለው ሚና የላቀ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ሚኒስቴሩ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም ለመጠቀምና ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ለውድድሩ ከ11 ክልሎች የሚሳተፉ ከ2 ሺህ 600 በላይ ተወዳዳሪዎች ወላይታ ሶዶ ከተማ የገቡ ሲሆን፤ ወጣቶቹ በ11 የውድድር ዓይነቶች እንደሚሳተፉም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።