“ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው” :- አቶ አደም ፋራህ

You are currently viewing “ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው” :- አቶ አደም ፋራህ

AMN- ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

ሀገራዊ ህልም ዕውን እንዲሆን እንደሀገር ባስቀመጥናቸው የጋራ ህልም ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የራሳቸውን ገንቢ ሚና መወጣት አለባቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።

የምክር ቤት አባላት ካለባቸው ሕዝባዊ ኃላፊነት አኳያ የሀገር ህልም እንዲሳካ ከፍተኛ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በሚከታተሏቸውና በሚቆጣጠሯቸው ተቋማት እና በመራጭ ህዝባቸው ውስጥ እንዲሠሩ ያስፈልጋል፤ ይህን መነሻ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ አደም ይህን የገለጹት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቶች አመራሮች እየተሰጠ ባለው ሥልጠና ላይ ነው።

አቶ አደም ለሰልጣኞች ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “የህልም ጉልበት፤ ለእመርታዊ ዕድገት” በሚል መሪ ርዕስ በቀረበው ገለፃ ላይ ከሰልጣኞች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ አደም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያደርሳትን እና ለትውልድ የሚሻገር ህልም ተልማለች፤ ይህ ህልም እውን ይሆን ዘንድም ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎች አሏት ብለዋል።

በመሆኑም የሀገራችንን መበልፀግ እውን ለማድረግ የጋራ ህልም ሊኖረን የሚገባ ሲሆን፤ ህልማችን በረጅም ግዜ የሚሳካ በመሆኑ ህልማችን እውን ይሆን ዘንድ ኃላፊነታችንን በተገቢው ደረጃ መወጣት አለብን ሲሉ ገልፀዋል።

ህልምን ህያው ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ትክክለኛ ሐሳብ መሆኑን የገለፁት አቶ አደም የመደመር ሐሳብ ኢትዮጵያን ከማሻገር አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጭምር የሚተርፍ መሆኑንም አብራርተዋል።

አያይዘውም ሀገሪቱ ያላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ከዓላማው ጎን የሚሰለፍ ሕዝብ እንዲሁም የተገነቡ ተቋማት የሀገራችንን ህልም ዕውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች ከሚባሉት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆኑን አስረድተዋል።

ህልም የጋራ መረዳትና ርዕይ ጋር የተገናኘ እንደሆነና በምናቅዳቸው ዕቅዶች፣ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎችና በምንሠራቸው ሥራዎችና ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ይህን ህልም ዕውን ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉ ክቡር አቶ አደም ጠቁመው፤ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቋቋም የአመራሩ ፅናት፣ የሐሳብና የተግባር አንድነት መኖር፣ ከሕዝብ ጋር በትስስር መሥራት እና የጋራ ህልማችንን በመደመር ዕሳቤ በሕዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት ወሳኝ ናቸው ሲሉም ነው አቶ አደም ያስገነዘቡት።

በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህልምን አስመልክቶ በቀረበው ገለፃ መሠረት ቻይናን ጨምሮ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት ለእድገታቸው መሠረት የሆነ ህልም እንዳላቸው ሁሉ ኢትዮጵያም ወደ ብልፅግና የሚያሻግራት የጋራ የሆነ ህልም አስፈላጊ መሆኑ ተብራርቷል።

ህልም ከትላንት ይልቅ ዛሬ ላይ፣ ከዛሬ ይልቅ ደግሞ ነገ ላይ የሚያተኩር፣ አንዱ ትውልድ የሚጀምረው፣ ቀጣዩ ትውልድ የሚኖረው እንደሆነም ነው የተገለፀው።

የሀገሪቱ ህልም ዕውን የመሆን ትልቅ ተስፋ ከወዲሁ እየታየ መሆኑ፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በለውጡ ውስጥ የገጠሙንን ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ከፍተኛ ዕድገት እያሰመዘገበ መምጣቱን በተለይም ከባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ እንደሆነም ነው የተገለፀው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ቡናን ጨምሮ የሀገሪቱ የግብርና ምርቶች በዓለም እና በአፍሪካ የቀዳሚነት ደረጃን እየያዙ መምጣታቸው፣ አለምን ያስደነቀ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች መሠራቱ፣ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ መድረሱ፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣ የኮሪደር ልማት መስፋፋት ማሳያዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

ህልም ዕውን እንዲሆን በጋራ መሥራት እንደሚገባም አንስተው የአመራሪ ፅናት፣ ቁርጠኝነት፣ በመተማመን እና በትብብር መስራት እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review