
AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በ9 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አጀንዳን በህዝባዊ ውይይቶች መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
በቅርቡም በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት አጀንዳን እንደሚሰበስብም አመልክቷል፡፡

በዚህ ሂደት ባለድርሻ አካላት ተብለው የተለዩት እና ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ውስጥ እያሳተፋቸው የሚገኙት አካላት በየወረዳው ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ ተወካዮች ፣ የሃይማኖት ተቋማት ፣ የመምህራን ማህበር ፣ የሲቪል ማህበራት ፣ ክልላዊና ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የአሰሪዎች ማህበራት ፣ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፣ የሙያ ማህበራት ይገኙበታል ፡፤
የክልል መንግስት (አስፈጻሚ አካላት) ፣ የክልል ዳኞች ፣ የክልል ምክር ቤት ፣ ታዋቂ ሰዎች ፣ የሚዲያ ተቋማት (ጋዜጠኞች) ማህበር ፣ የቀድሞ ሰራዊት ማህበራት ፣ የንግድ ማህበራት ምክር ቤት ፣ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራት ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ፣ የመንግስት ሰራተኞችም በምክክሩ እየተሳተፉ መሆኑን ኮሚሽኑ በመረጃው አመልክቷል፡፡