
AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም
ሀገራዊ የወል ህልሞችን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የመንግስት ሰራተኞች በሀገር ወዳድነት ስሜት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የተመሰረተበትን 5ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከህዝብ ተወካዮች እና ከፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሰራተኞች ጋር “የህልም ጉልበት፤ ለእምርታዊ እድገት” በሚል ርዕስ ውይይት ተካሒዷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ በውይይቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካ ንቅናቄ፣ ንግግሮችና ትግሎች ከተጀመሩ 70 አመታት ማስቆጠራቸውን አንስተዋል፡፡
ለእነዚህ የፖለቲካ ንቅናቄዎች መነሻ ከነበሩ አበይት ጉዳዮች መካከል ዴሞክራሲ፣ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ንቅናቄዎቹ በየዘመኑ የስርዓት ለውጥ ያመጡ ቢሆንም የህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለይቶ ምላሽ ከመስጠት አኳያ ችግሮች እንደነበሩባቸው አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሰልቺ እና አድካሚ የፖለቲካ ድግግሞሾችን ካሳለፈች በኋላ ከስድስት አመት በፊት ከውስጥ እና ከውጭ በተደረጉ ትግሎች የለውጡ መንግስት መመስረቱን ገልጸዋል፡፡
ለውጡም በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ እንዲጀመርና መጠነ ሰፊ የሪፎርም ስራዎች በማከናወን በሁለንተናዊ ዘርፎች ስኬቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በለውጡ ማግስት ዘመኑን የዋጁ ተቋማት መገንባታቸውን፣ ሐቀኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት መተግበሩን ፣ የተሟላ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ፖሊሲ ማዕቀፍ እውን መሆኑንና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት ተግባራዊ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም ሀገራዊ የወል ህልሞችን እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል በመሆኑ በተለይም የመንግስት ሰራተኞች በሀገር ወዳድነት ስሜት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፤ በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ተጨባጭ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም ከመጣንበት በተሻለ ፍጥነት የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስት ሰራተኛው ትልቅ ሃላፊነት ያለበት መሆኑን አውቆ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ፤ በበኩላቸው የመንግስት ሰራተኞች የመንግስት ፖሊሲዎችን የማስፈጸም ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
የወጡ ህጎችን፣ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችንና መመሪያችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚከናወኑ ሒደቶች ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።
የዜጎች ቀዳሚ ፍላጎት ዘላቂ ልማትና ሰላም መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የመንግስት ሰራተኛው የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።