AMN – መስከረም 28/2017 ዓ.ም
ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ከመንግስት እና ከግል ሚድያ ጋዜጠኞች ለተነሱልኝ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሰጠ የስራ መመሪያ መሰረት የተጠኑት የሁለተኛ ዙር ኮሪደሮች ስምንት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
“ለህዝብ ያለእረፍት እየሰራን ከህዝብ የምንደብቀው ምንም ስለሌለ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቻለሁ። ማብራሪያ መስጠቱ ለወደፊትም ይቀጥላል” ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ዋና አላማዉ ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፤ ገፆታዋን ማሻሻል እና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በአጠቃላይ 2817 ሄክታር መሬት በሚሸፍን እና 132 ኪ.ሜ ርዝመት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባ መሆኑን ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡
በግንባታ ስራው ከተካተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎች ውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የታክሲና አውቶቢስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች፣ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የህዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ፣ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ መብራት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት እንዲሁም የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ ስራ ተጠቃሾቹ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ስራው በዋናነት በከተማው አቅም እና በጀት የሚከናወን መሆኑ የተገለጸ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፤ የመብራት አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በዚህ ውስጥ መሰረተ ልማታቸውን በመዘርጋትና ከተማዋን ስማርት ሲቲ በማድረግ በኩል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉ ከንቲባዋ አመላክተዋል፡፡
ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል፡፡
በመልሶ ማልማት ሲኖሩ ከነበሩበት ለመኖር ምቹ ያልሆነ ጎስቃላ አካባቢዎች ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን፣ በቂ የመስሪያ ሼዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም ከ 500 በላይ የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን ለነዋሪዎች ዝግጁ መደረጉን ከንቲባዋ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ምትክ መሬት እና ካሳ አዘጋጅተናልም ብለዋል።
በሁለተኛ ዙር የተለዩት ኮሪደሮች:-
1.ካሳንቺስ- እስጢፋኖስ-መስቀል አደባባይ- ሜክሲኮ- ቸርችል-አራት ኪሎ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራ (የኮሪደሩ ርዝመት 40.4 ኪ/ሜ)
2. ጫካ ፕሮጀክት (ሳውዝ ጌት)- መገናኛ- ሃያ ሁለት- መስቀል አደባባይ ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 7.1 ኪ.ሜ)
3. ሲኤምሲ- ሰሚት- ጎሮ- ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደር እና የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 10.8 ኪ.ሜ)
4. ሳር ቤት- ካርል አደባባይ- ብስራተ ገብርኤል- አቦ ማዞሪያ- ላፍቶ አደባባይ- ፉሪ አደባባይ ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 15.9 ኪ.ሜ)
5. አንበሳ ጋራዥ- ጃክሮስ- ጎሮ ኮሪደር ( የኮሪደሩ ርዝመት 3.1 ኪ.ሜ)
6. አራት ኪሎ- ሽሮ ሜዳ- እንጦጦ ማርያም- እጽዋት ማዕከል ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 13.19 ኪ.ሜ)
7. ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 20 ኪ.ሜ)
8. እንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 21.5 ኪ.ሜ)
ከላይ የተዘረዘሩ ኮሪደሮች ምዕራፍ በምዕራፍ ተከፍለው በጥራት እና በፍጥነት እንደሚሰሩም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የትራፊክ መጨናነቅን ጨምሮ የሚኖሩ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን በመቻል እንደ መጀመሪያው ዙር በትብብር ከተማችንን በጋራ እንድንገነባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡