ሁለተኛው ዙር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

You are currently viewing ሁለተኛው ዙር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ
  • Post category:ልማት

AMN – ሀምሌ 5/2016 ዓ.ም

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በስምንት ክልሎች ተግባራዊ የሚደረገውን ሁለተኛው ዙር የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

በሀዋሳ ከተማ የፕሮጀክቱ የማስጀመሪያ አውደ ጥናት እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 424 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት እንደተያዘለት ተጠቁሟል።

በዚህ ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ የአርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የተዘጋጀው ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረገው በስምንት ክልሎች ነው።

በዚህም በክልሎቹ የተመረጡ 120 ወረዳዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱ ዓላማ በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ህይወት ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ማጠናከር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የመሬት ለምነትን በዘላቂነት በመጠበቅ የእንስሳት መኖ ልማት፣ የሰብል እና የአትክልት ምርታማነት ማሻሻል የሚረዱ ተግባራት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ መረጃ በመስጠት የድርቅ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በአርብቶ አደሩ አካባቢም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማረጋገጥም ይረዳል ብለዋል።

በዚህም 600ሺህ አባወራዎችን ጨምሮ ሦስት ሚሊዮን ቤተሰቦቻቸው የፕሮጀክቱ ቀጥታ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ሁለት ሚሊዮን የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በፕሮጀክቱ ከ30 እስከ 50 በመቶ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሪያስ ጌታ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት ተገኝተዋል።

እንዲሁም ፕሮጀክቱ በሚካሄድባቸው ድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ ከአፋር፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የልማት አጋር ተቋማት ተወካዮችም ተገኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review