ሁለት ተሽከርካሪዎችን ይዞ የተሰወረው የጥበቃ ሰራተኛ ከግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ዋለ

You are currently viewing ሁለት ተሽከርካሪዎችን ይዞ የተሰወረው የጥበቃ ሰራተኛ ከግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ዋለ

AMN- ሚያዝያ 23/2017 ዓ.ም

ሁለት ተሽከርካሪዎችን ከሚጠብቅበት ድርጅት ይዞ የተሰወረው የጥበቃ ሰራተኛ ከግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ/ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ጋድ ኮንስትራክሽን ግቢ ውስጥ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ እንደሆነ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኤኤምኤን ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት፣ በዕለቱ ተረኛ የነበረው የድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኛ የተሽከርካሪዎች ቁልፍ እሱጋ የመቀመጡን አጋጣሚ በመጠቀም ከሌሎች 8 ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ግምታቸው 6.6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ተሽከርካሪዎችን ይዘው መሰወራቸውን ገልጸዋል፡፡

የሠሌዳ ቁጥራቸው ኮድ3 – 55363 አ/አ እና ኮድ 3-A06106 አ/አ የሆኑ ሁለት ተሽከርካሪዎችን ከድርጅቱ በመስረቅ ወደ ሀዋሳ ቀጥሎም መዳረሻቸውን ወላይታ ሶዶ ከሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በኋላም ደላላ በመጥራት ፒካፕ ፎርድ የሆነውን ተሽከርካሪ በ900 ሺህ ብር ለመሸጥ በመስማማት፣ ግዢውንም 2 መቶ ሺህ ብር በእጃቸው፣ 2 መቶ ሺህ ብር በቼክ የፈጸሙ ሲሆን፣ ቀሪ 500 ሺህ ብሩን ደግሞ ስም ካዘዋወሩ በኋላ ሊሰጣቸው መስማማታቸውን ፖሊስ መምሪያው መግለጹ ተመላክቷል።

ፖሊስም፣ የህብረተሰቡን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ ዋና ወንጀል ፈፃሚውን፣ የወንጀሉ ተባባሪዎችን እንዲሁም ተሽከርካሪውን የገዛውን ግለሰብ ጭምር ጋራዥ ቀለም እያስቀየረ በነበረበት በቁጥጥር ስር በማዋል ሁለቱንም ተሽከርካሪዎች የማስመለስ ስራ መስራት መቻሉን አመላክተዋል፡፡

አሁን ላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ኮማንደር ማርቆስ ገልጸዋል።

የጥበቃ ሰራተኛው ሲቀጠር በቂ ተያዥ ያልነበረው መሆኑን በመግለጽም፣ ድርጅቶችም ሆኑ ተቋማት የጥበቃ ሰራተኛ ሲቀጥሩ በቂ ተያዥ ያላቸው ግለሰቦችን መቅጠር እንዲሁም ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review