ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተለይም በአፍሪቃ ቀንድ በአብዛኛዉ ቅንነት እና የጋራ ተጠቃሚነትን ከግምት ዉስጥ ያስገባ ነው። ይኽ አይነት አዎንታዊ የፖሊሲ አካሄድ መነሻው በአብዛኛው የቀናይነት እሴት የተላበሰዉ ህብረተሰብ እና የመሪዎች ዕይታ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያ ከጥንተ ታሪኳ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ማንንም ሀገር ለመዉረር ሙከራ አድርጋ የማታውቅ፥ ነገር ግን አልፈው ሲመጡባት በበቂ ሁኔታ ህዝቧን እና ሀብቷን አንቀሳቅሳ አሳፍራ መመከቷ ነው፡፡
እንዲያው የሩቁን ታሪክ ትተን በቅርቡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አጋጥሞን የነበረውን ግጭት ከግምት ዉሰጥ በማስገባት ‘የኢትዮጵያ የሀይል ሚዛን ተዛብቷል’ ብላ ስታስብ ሱዳን ቀድሞ ‘ይገባኛል’ በሚል ስትጠይቅ የነበረውን የአልፈሻጋን መሬት በሀይል መውረሯ፤ በተቃራኒው ደግሞ ሱዳናዊያን በገጠማቸው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ከቦታው (ከአልፈሻጋ) የሱዳን ወታደር ሲለቅቅ እንኳን በሀይል የቀድሞ ግዛታችንን ለማስመለስ ይቅርና ጭራሽ የሱዳን ህዝብ ወንድም ህዝብ ስለሆነ ችግሮቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ትልቅ ሃላፊነት የወሰደው የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡
ታዲያ ይኽ አካሄድ tit-for tat (የተደረገብህን ነገር በተመጣጣኝ ግብረ – መልስ መመለስ) የሚለዉን ነባር አስተሳሰብ አፋልሶ “ክፉ ላደረገብህ መልካም ስራ” በሚለዉ እሳቤ መመለሱ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተቀነበበዉ በቅንነት ላይ የተመሠረተ እሳቤ ነው የሚለዉን የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ “ቢሆን”ን የሚያጠናክር ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ይኽ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረዉ እና መነሻዉ ከሰፊዉ ቀናኢ ማበረሰባዊ ስሪት እሴት የሚቀዳዉ የዉጪ ጉዳይ ፖሊሲያችን ያስገኘዉ ጥቅም እና ኪሳራ ተሰልቶ እና በሚገባ ተለይቶ ማስቀመጥ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ከሩቅም ከቅርብም፥ ትንሹም ትልቁም ሀገር ብሄራዊ ጥቅሙን ለማስከበር እና ለማስጠበቅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ደባ እና ተንኮል እየፈጸመ እኛ በቅንነት ነገሩን ማየት እስከምን ድረስ ይወስደናል? አሁን እኛ እንደ ሀገር ካለንበት የዉስጥና ቀጣናዊ ጉዳዮች እንፃር ልንከተለዉ የሚገባው የፖሊሲ እይታ ምን መሆን አለበት? ለሚለዉ ጥያቄ ምክረ-ሀሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በዚህም የአካዳሚያዉያን የውጪ ፖሊሲ እይታዎቻቸዉን ከቀጣናዉ ሀገራት ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት እንደሚከተለዉ በሶስት ዋና ዋና ማንፀሪያ ከፍዬዋለሁ፤
1ኛ- ደበኝነት(cynical and intrigue driven Fop outlook)
2-ኛ- ገርነት (optimistic and shared values driven Fop outlook)
3ኛ-ገር-ደበኝነት (critical Fop outlook)
- ደበኝነት(cynical and intrigue driven Fop outlook)፡-
ይኽ የዉጪ ጉዳይ ፖሊሲ አማራጭ በዋነኝነት የሚነሳዉ ከተጨባጩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ደህንነታዊ ሁነት ሲሆን፤ ምስራቅ አፍሪቃ ሀገራት መገለጫ የሆኑትን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀዉስ፣ የሰላም እና መረጋጋት እጦት፣ አሸባሪ ቡድኖች የደቀኑት ተጨባጭ እና አይነተ ብዙ የደህንነት ስጋት፣ የከባቢ አየር ንብረት ለዉጥ የደቀነዉ ተደጋጋሚ ድርቅ እና የዲሞክራሲ እጦት የወለደዉ መንግስት እና ሀገረ-መንግስት የቅቡልነት ዕጦትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የራስን ፍላጎት ኢ-ሞራላዊ እና አፍራሽ በሆነ መንገድ ማሳካትን ታሳቢ ያደረገ የዉጪ ጉዳይ ፖሊሲ እይታ ነው፡፡
ተጨባጩን የቀጣናው አሁናዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት “ጥቅም አለኝ” የሚሉ የአካባቢውም ይሁን ከውጪ ያሉ ሀገራት ቀጣናዉን ለማተራመስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፥ በፖለቲካ ምክንያት ወይንም በሌላ ያኮረፉ ቡድኖችን በመደገፍ ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር በማድረግ፤ ህዝቡ እና የቀጣናው ሀገራት መንግስታት ከልማት እና ከብልፅግና ላይ እንዳያተኩሩ በማድረግ፤ ህዝቡን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ረፍት በመንሳት አለኝ ያሉትን ጥቅም ማስጠበቅ ይቻላል የሚል የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እይታ ነው፡፡ በዚህ ፖሊሲ እሳቤ የቀጣናዉም ይሁን ከዚያ ውጪ ያሉ ሀገራት በፈጠሯቸው የታክቲካል አሰላለፍ እና አዳዲስም ይሁን የነበሩ ወታደራዊ ስምምነት(ከቀጣናው መንግስታት፣ ከጎሳዎች፣ ኢ-መደበኛ ከሆነ አደረጃጀት) በማድረግ እና እንደ አዲስ በማደስ፤ በዚህም አማካኝነት ጥቅማቸውን ሲያስጠብቁ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ፖሊሲ ተፈፃሚነት ትልቁ እና አስተማማኝ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረዉ በቀጣናው ያለው ውስብሰብ፤ ብዙ እጅ ያለበት የብዙ ተዋንያን ፍላጎት የፈጠረው አለመረጋጋት ነዉ፡፡
የዚህ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ብሂል የወለደው የፖሊሲ ዕይታ ትልቁ ችግር የአጭር ጊዜ ግብን አላማ ያደረገ እና ኢ-ሞራላዊ በሆነ መንገድ ብሄራዊ ጥቅምን ማሳካት ከግምት ውስጥ ያስገባ ሆኖ እናገኘዋለን። እዚህ ጋ እየተነጋገርን ያለነዉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገረውን ቋሚ ብሄራዊ ጥቅምን የማሳኪያ መንገድን ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ‘ተዳክሟል፤ እርስ በእርሱ እየተናጨ ነው’ ያልነው ሀገር የዉስጥ ችግሩን የሚፈታ ጥበበኛ እና አስተዋይ ትውልድ ሲነሳ መልሶ የተወሰደበትን ጥቅም በሀይል ለማስመለስ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የግጭት አዙሪት ውስጥ በመክተት በደባ የተጠበቀውን፣ የተገኘዉን ብሄራዊ ጥቅም በዜሮ ድምር ውጤት በመደምደም ግጭትን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር የማንም ጥቅም እነዳይጠበቅ ያደርጋል፡፡ ለአብነትም ሰሞኑን ‘ኪንግ ኦፍ አባይ’ በሚባለዉ የዩቲዩብ ሚዲያ ላይ በተተረጎመ እንድ ዝግጅት ላይ የቀድሞ የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣን እንዴት ከዚህ ቀደም የነበሩትን የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎችን ከካይሮ ጋር በማበር ሲረዱ እንደነበረ ሲገልፁ፡-
”አራት ኪሎም ይሁን አስመራ የገቡት ሁለቱም ሀይሎች( ህወሓት እና ሻዕቢያን ማለታቸው ነው) ይነዱት የነበረው ታንክ፣ ይተኩሱት የነበረው ጥይት የእኛ ነው፡፡ ታንኩ የኛ፣ ሹፌሩ ሀበሻ ነዉ” በማለት ነበር፡፡
ይኽ ደባዊ እና ፍላጎትን በጣልቃ ገብነት የማስፈፀሚያ ፖሊሲ ለጊዜዉ ውጤት አስገኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጥቅምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚችል አካሄድ አለመሆኑን አሁን በዚህ ሰዓት ሱዳን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በማየት መረዳት ይቻላል። የረዳውም የተረዳዉም መንግስት ቢያንስ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ህዝብ ስልጣን ላይ እይደሉም። በዚህ ፖሊሲ ጥቅምን በዘላቂነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ማሳካት ባይቻልም የሚያስከትለው ጉዳት ግን እንደየሁኔታው ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢያንስ ኢትዮጵያን ወሳኙን የባህር በር እና መተንፈሻ በማሳጣት የዚህ ትውልድ የቤት ስራ እንዲሆን አድርጓል፡፡
2. ገርነት(optimistic and shared values driven Fop outlook)
የጋራ ተጠቃሚነትን ከግምት ውስጥ የሚያስገባው “ገርነት” በሚል የሰየምኩት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በዋነኛነት የእሳቤ መነሻው፥ “ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠዉ የህዝቦችን እና የጎረቤት ሀገሮችን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው” ከሚል ነው። ሁሉም ሊባል በሚቻል ደረጃ የቀጣናው ሀገሮች የውስጥ ፖለቲካዊ ችግር ቢኖርባቸዉም በባህልም፣ በድንበርም ብዙ የጋራ እና ሚያመሳስሏቸው እሴት ያሏቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የአንዱ ሀገር ችግር የሌላዉ ሀገር ችግር መሆኑ ስለማይቀር ብሄራዊ ጥቅምን በመነጋገር በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ ማሳካት ይቻላል ብሎ የሚያምነው ገራገር የፖሊሲ አማራጭ ነው። ከዚህ አንጻር ስናየዉ ምንም እንኳን የየራሳቸዉ ክፍተት ቢኖርባቸዉም ኢትዮጵያን የመሩት መሪዎች የዚህ ፖሊሲ ተጠቃሚ ናቸዉ ብሎ መዉሰድ ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያን አሁናዊ ሚና በቀጣናው በወፍ በረር መመልከት አሁን ስላለው የቀጣናው የሀይል አሰላለፍ እና የውጪ ጉዳይ ፖሊሲን ለመመልከት ዳራ ይሆነናል። በቀጣናዉ ያሉ ጎረቤት ሀገሮች ፖለቲካዊም ይሁን የደህንነት መናወጥ ሲገጥማቸው ኢትዮጵያ እድሉን ለአጭር ጊዜ እና ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ከመጠቀም ይልቅ ችግሮችን በንግግር እንዲፈቱ በማደራደር ትልቅ ሚናን ተጫውታለች፤ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን የተጫወተችዉ ሚና የዚህ ፖሊሲ ትሩፋት እና መገለጫ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሶማሊያ በዚያድ ባሪ የስልጣን ዘመን ወረራ የፈፀመች፣ በግልፅም ይሁን በድብቅ የመንግስትን ተቃዋሚዎች ስትደግፍ የነበረች ሀገርን ከአሊተሀድ እስከ አልሸባብ ድረስ ለተደቀነባት ሁሉን አቀፍ የደህንነት ስጋት ዉድ ልጆቻችን መስዋዕት በማድረግ ወንድም ሶማሌን ህዝብ ሰላም በማረጋገጥ፣ ሶማሊያ የተረጋገች እና የበለፀገች ጎረቤት እንድትሆን ኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡
ታዲያ ከቂምና ከደባ ነፃ የሆነውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመከተል ምን አሳካን? ብለን ብንጠይቅ፤ ዛሬ ላይ የውድ ኢትዮጵያዊ ጀግኖችን መስዋዕትነት የረሳ፣ የቀጣናው አባል ሀገር ላልሆኑት እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ነጭ ለባሽ ሆኖ በማገልገል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለመጉዳት የሚሮጠዉን የሶማሊያ መንግስት ፖሊሲ የተቃወሙት ሶማሌ-ላንድ፣ የፑንት ላንድ፣ የሄርሸባሌ እና ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ክልሎችን ስንመለከት የተከፈለዉ ዉድ የሰው ህይወት፤ በገርነት እና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር ፖሊሲን በመከተል በዘላቂነት የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይኽ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ሶማሊያ ውሰጥ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ባህሪ ምንም ይሁን ምን ኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ህዝብ ጥቅማቸውን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በጋራ አንዲቆሙ እነደሚያስችል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለዚህም ነው ከሰሞኑ ካይሮን እና ሶማሊያ መንግስትን አፍራሽ ወታደራዊ ህብረት በመቃወም ሰልፍ ወጥተው ለኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ያላቸዉን ድጋፍ በግልፅ ያሣዩት፡፡ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ግንኙነት ለዚህ የአትዮጵያ ፖሊሲ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ከላይ የተቀመጡት አዎነታዊ ጎኖቹ እንዳሉ ሆነው በሌላኛው በኩል ትብብርን እና የጋራ ተጠቃሚነትን የማይቀበል መንግስት ስልጣን ሲቆጣጠር በቋሚነት የቀጣናው በጥባጭ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፤ በተጨማሪ ከቀጣናው ውጭ ላሉ ሁከት እና ግጭት ጠማቂዎች እጅ እና እግር በመሆን በትብብር አብሮ ማደግን ያስቀደመችው የኢትዮጵያን ጥቅም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚጎዳ ሀገር መንግስት፤ በሌላ በኩል ይኽ የእኩይ ባህሪ ባለቤት የሆነው መንግስት በሚፈጥረው የአፈና ኔትዎርክ ምክንያት ህዝቡን ለእኩይ አላማ ማስነሳት ከቻለ በዚህ ገራገርነት የሚመራዉ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ብሄራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነዉ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው፡፡ ስልጣን ላይ ያለዉ የኤርትራ መንግስት በሚከተለዉ ፍፁም የተሳሳታ የውጭ ጉዲይ ፖሊሲ ምክንያት ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲገለል እና ወንድም የሆነውን የኤርትራ ህዝብ አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለው እንደነበረ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህ ከዓለም እና ከቀጣናው ህዝብ የተነጠለ እና የስትራቴጂክ ስህተት መገለጫ በሆነው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክንያት የቀጣናው ቋሚ በጥባጭ እንዲሆን አድርጎታል። ኢትዮጵያን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት አብዛኞቹ ሊባሉ የሚችሉ ተቃዋሚዎች መገኛቸው ኤርትራ እንደነበር ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ በፈጠረው ያላሰለሰ እና ድፍረት የተሞላበት ጥረት እና የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዕይታ ለ20 ዓመታት ተፈጥሮ የነበረዉን ያለመግባባት በሰላም ለመፍታት ተችሎም ነበር፡፡
በዚህም ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተገፍቶ እና ተገልሎ የነበረዉ የኤርትራ መንግስት ለጥቂት አመታት ወደ አለም ፖለቲካ መድረክ የተመለሰ ቢሆንም ስሪቱ ነውና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጠሩ የትኛውም አይነት ፖለቲካዊ ያለመረጋጋቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጣልቃ እየገባ መበጥበጥ የሆነውን ቀደምት ባህሪ ፈፅሞ ሊተወው አለመቻሉን እና በተለያየ ደረጃ ሊገለጥ የሚችል በግልፅ እና በህቡዕ መንገድ እየደገፈ እንደሚገኝ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለዉ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ከላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው የጋራ ተጠቃሚነትን ከግምት ውሰጥ ያስገባ ነው፡፡ ይኽን ፖሊሲ ሊቀበል ከማይችል መንግስት ጋር ልንከተለው የሚገባው ፖሊሲ ገራገርነት የተሞላበት ከሆነ በእጅጉ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እዚህ ጋ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልችለው ጉዳይ ምንም እንኳን መንግስት በራሱ ሊያቀርበው የሚችለው ምክንያት ቢኖረዉም እኔ የኤርትራ መንግስት በቀጣናው ላይ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ (በኢንፎርሜሽን ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከሚሰጡት መረጃዎች አንጻር) የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ እና መንግስት ብሄራዊ ጥቅም ጠላት ተብሎ ሊያስፈርጅ ይገባዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ እሳቤ የሚቀዳ የዉጭ ፖሊሲ እይታ እና አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይኽ ሁኔታ ወደ ሶስተኛዉ የፖሊሲ አማራጭ ያመራናል፡፡
3. ገር-ደበኝነት(Critical and pragmatic outlook )
ገር-ደበኝነት የሚለዉ ቃል (ገር+ደባ) ከሚለዉ ቃል የተወሰደ ሲሆን በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ሁለቱ ቃላት ሚወክሉትን ባህሪያት አዋህዶ የያዘ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ ይሄኛዉ የፖሊሲ አማራጭ ከላይ የተጠቀሱትን አማራጮች እንደ ጎረቤቶቻችን የፖሊሲ ታሪክ እያፈራረቀ የሚጠቀም ነው፡፡ ዘላቂ የሆነዉን የሀገራችንን ጥቅም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በማተኮር ለማሳካት የሚጥር፣ በሌላ በኩል ጥቅም አለኝ በሚለው የትኛውም ጎረቤት ላይ ደባ ሲሰራ እና ሲፈፅም ለነበረ፣ ሲችል እና ሲሳካለት ደግሞ በቀጥታ ወረራን ለሚፈፅም መንግስት፤ ለዚሁ አላማ መሳካት ህዝብን ማስተባበር የሚችል መንግስት ልንከተለው የሚገባ የፖሊሲ አቅጣጫ በግልፅ እና በማያሻማ መልኩ tit for tat ሊሆን ይገባል፡፡ ለተደረገብን እና ለሚደረግብን ሁሉ እኩል እና ተመጣጣኝ ግበረ-መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የውስጥ ተቃዋሚዎችን የሚረዳ፣ ለታሪካዊ ጠላቶች እጅ እና እግር ለመሆን የሚሰራ፣ ቀጣናው እንዲረጋጋ የጥኛውም ሀገር መንግስት ጋ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ አተኩሮ መስራት መለወጥ የማይችልን ነገር ለመለወጥ መሞከር አድካሚ እና አታካች ነው፡፡ ስለዚህ ኤርትራ ዉስጥ ተቃዋሚዎችን ማደራጀት፣ ማስታጠቅ፣ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲገለል መስራት፤ የህዝብን ጥቅም በዘላቂነት፣ በመተባባር እና በጋራ ተጠቃሚነት ለማሳካት የሚያምን ቡድን እንዲፈጠር መስራት እና ሲፈጠር ደግሞ ገርነት ፖሊሲን መጠቀም አስፈሊጊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ ይሰጣል የምንለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን በመርህ ደረጃ ትክክል ቢሆንም ለሁሉም ጎረቤቶቻችን እኩል የሚሰራ መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ ይኽን የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሥቀድም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቀበል የሚችል ጎረቤት ሀገር እና መሪ ሲኖር በዘላቂነት ብሄራዊ ጥቅማችንን ማስከበር እንችላለን፡፡
ነገር ግን የሰለጠነዉን እና በዘላቂነት ብሄራዊ ጥቅምን ማሰካትን ግብ ያደረገዉን ውጭ ጉዲይ ፖሊሲ ሊቀበል የማይችል እና ኋላቀር መንግስት(የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ዓይነት) ላይ ግን በራሱ መንገድ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሰሞነኛው የምስራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ እድገቶችን ስንመለከት ኢትዮጵያ ልትከተለው የሚገባው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በጎረቤቶቻችን መካከል መተማመንን የሚያጠነክር፤ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ቀጣናዉን ለማተራመስ የመጡ በዙሪያቸው እና አፍንጫቸው ስር ያለውን አሁናዊ እና ተጨባጭ የደህንነት ስጋት መፍታት ያልቻሉ ሀገሮች እና ለእነዚህ ሀገሮች ነጭ ለባሽ ለሆኑት ሀገራት የምንከተለው ፖሊሲ ጥበብ
የተሞላበት፣ በትክክል ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ከህዝቡ እና ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ መነጠልን ኢላማ ያደረገ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ከውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ቅራኒዎችን በፖለቲካዊ መንገድ በመፍታት የሀገራችንን ሉአላዊነት በማይናወጥ አለት ላይ መመስረት አስፈሊጊ ነው፡፡
በአሌክስ ብርሀኑ ሙልጌታ
የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ
ኢሜይል alexbirhanu81@gmail.com