
AMN- ግንቦት 16/2017 ዓ.ም
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓ ህብረት ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ ለመጣል መዘጋጀታቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት የህብረቱን ጥቅም ሊጎዳ የሚችል ነገር እከላከላለሁ ሲል አስታውቋል፡፡
የአውሮፓ ህብረትን የንግድ ዘርፍ የሚመሩት ማሮስ ሰፍኮቪች ትናንት በኤክስ ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ ” የአውሮፓ ህብረት የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም የሚያስከብር ስምምነት ለማድረግ ቁርጠኛ ነው፤ የአውሮፓና አሜሪካ ንግድ በጋራ ተጠቃሚነት እና መከባባር እንጂ በመጎዳዳት መርህ ሊመራ አይገባም፤ ህብረቱ እራሱን ለመከላከልም ዝግጁ ነው” ብለዋል፡፡
ዓለምን በቀረጥ ማዕበል ማናወጥ የተያያዙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ በህብረቱ ሥር በሚገኙ 27 አባል ሀገራት ላይ 50 በመቶ የሚሆን ቀረጥ እንደሚጥሉ በማህበራዊ ትሥሥር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ከህብረቱ ጋር ለዚህ ተብሎ የሚደረግ ድርድር ካለም እንደማይታገሱ ነው የገለጹት፡፡
ምንም እንኳን አውሮፓ ወሳኝ የንግድ አጋር ብትሆንም፣ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ቀረጡ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡
ምናልባት የአውሮፓ ትላልቅ ኩባንያዎች በአሜሪካ ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚያካሂዱ ከሆነ ብቻ የቀረጥ ትግበራው ጉዳይ ሊራዘም ይችላል ማለታቸውን አልጀዚራ ነው የዘገበው፡፡
በማሬ ቃጦ