ህዝቡ ለአንድነት፣ ለሰላምና ለፍቅር መትጋት ይኖርበታል- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

You are currently viewing ህዝቡ ለአንድነት፣ ለሰላምና ለፍቅር መትጋት ይኖርበታል- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

AMN-ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም

ህዝቡ አንድነትና ፍቅሩን በመጠበቅ ለአገር ዘላቂ ሰላም መትጋት እንዳለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ።

በፓትርያርኩ የተመራ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ቡድን ከነገ በስትያ ለሚከበረው ለቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ንግስ ክብረ በዓል ላይ ለመታደም ዛሬ ከሰዓት ድሬዳዋ ገብቷል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ተገኝተው ለፓትርያርኩ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የእምነት አባቶች ህዝበ ክርስቲያኑ ከፈጣሪው ጋር ያለውን ፍቅር እና ሕብረት ጠብቆ እንዲጓዝ በትጋት ያስተምራሉ፤ ይመክራሉ።

ህዝቡም ኃይማኖቱን፣ ምግባሩን እና ከአምላክ ጋር ያለውን ቅርበት በመጠበቅ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት መትጋት እንደሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር በጋራ ሰላም በመስራትና ለሚከሰቱ ችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት እያደረገ ላለው ትብብርም አመስግነዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ከተማ አስተዳደሩ ለቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል በዓል በድሬዳዋ በኩል ለሚመጡ እንግዶች አስፈላጊውን ድጋፍና መስተንግዶ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ፓትርያርኩ በድሬዳዋ ቅዱስ ዑራኤል ወበዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን በ20 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነውን ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ህንፃ ዛሬ ይመርቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review