ህይወት  አድን  ስጦታ

You are currently viewing ህይወት  አድን  ስጦታ
  • Post category:ጤና

ደም መለገስ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በመሠረቱ ደም ልገሳ ቀላል፤ ለጋሹንም የማይጎዳ ህይወትን ለማዳን የሚደረግ በጎ ተግባር ነው፡፡ በከባድ የጤና እክል ለሚሰቃዩ፣ ቀዶ ጥገና ለሚያደርጉ ወይም አሰቃቂ አደጋ ያጋጠማቸውን ሰዎች ጤና  ለማሻሻል ቁርጠኛ አጋርነትን የምናሳይበት ብሎም የሞራል ግዴታችንን የምንወጣበት አይነተኛ መንገድም ነው።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ብቻ ሳትሆን፣ እንደማንኛውም አዳጊ አገር በርካታ የጤናና ማህበራዊ ችግሮች ያሉባት ናት። በተለይ ለሴቶችና ህፃናት፣ በጦርነትና ሰው ሰራሽ አደጋ ለሚጎዱ ሰዎች እንዲሁም በከባድ በሽታዎች ለሚጠቁ ወገኖች ከፍተኛ መጠን ያለው ደም በየጤና ተቋማቱ እንዲገኝ የሚያስገድዱ ናቸው።

ደም ደግሞ ከየትም የሚገኝ ሳይሆን ሙሉ ፈቃደኛ ከሆኑና ደም በመለገስ የህሊና እርካታ ከሚፈልጉ ወገኖች ብቻ የሚሰበሰብ ነው። ለዚህም ነው ቀይ መስቀልና ጤና ሚኒስቴር ጭምር “ህይወትን እንታደግ” በሚል መርህና ሌሎች መሰል ጥሪዎች ዜጎች ደም እንዲለግሱ የሚያበረታቱት። እውነት ለመናገር “ደም መለገስ የፍቅር መግለጫ ነው” የሚለው እሳቤ ከፍ ያለ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ነው። ከደም ለጋሹ ምንም ሳይጎድል፣ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ የሚሰጥ እንደመሆኑ ብዙዎች ሊሳተፉበት የሚገባ ተግባር እንደሆነ በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች ይመክራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ስቴድየም አካባቢ በሚገኘው ደም ባንክ ለ39ኛ ጊዜ ደም የለገሱት
አቶ ተስፋሁን ገብረመድህን

በኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር መላሽ ገላው፣ ማንኛውም ዕድሜው ከ18 እስከ 65 ዓመት የሆነ እና ክብደቱ ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን “ጤናማ” ግለሰብ በየ3 ወሩ በቋሚነት ደም ለመለገስ ብቁ መሆኑን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የክልል ከተሞችን ጨምሮ 50 የደም ባንኮች ያሉ ሲሆን፣ የበዓል ቀናትን ጨምሮ በሳምንት 7 ቀን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ድረስ የለጋሾችን ደም ለመቀበል ክፍት ሆነው ይጠባበቃሉ። በእነዚህም አመቱን ሙሉ ከሳምንት እስከ ሳምንት ያለምንም ማቋረጥ ደም እንደሚሰበሰብ ያስታወሱት ዶክተር መላሽ፣ በአዲስ አበባ ከተማም ከተመረጡ ደም ተቀባይ የጤና ተቋማት ባሻገር 2 ቋሚ እና 11 ተንቀሳቃሽ የደም መሰብሰቢያ ክሊኒኮች በቋሚነት ደም የማሰባሰቡ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ከሳምንት ሳምንት ያልተቋረጠ የደም አሰባሰብ ስርዓት ቢኖርም በተለይ በፆም እና በበዓላት እንዲሁም በክረምት ወቅት ግን መቆራረጥና የሚፈለገውን ያህል ደም ያለማሰባሰብ ችግር እንደሚያጋጥም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በዚህም አቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም ችግር ያጋጥማል፡፡

በክረምት ለሚያገጥመው የደም እጥረት አንደዋነኛ መንስኤ የሚነሳው የትምህርት ቤቶች መዘጋት ነው፡፡ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ደም የሚገኘው ከትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ በክረምት ወቅት የሚዘጉ በመሆኑ ይህ ምንጭ ይቋረጣል፤ በመሆኑም የደም እጥረት ይከሰታል፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት ሲባል የኢትጵያ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ማህበር አስተባባሪነት በከተማዋ በተመረጡ አደባባዮችና በ15 የተለያዩ አካባቢዎች ድንኳን ተተክሎ ከጠዋት እስከ ማታ ደም የማሰባሰብ ስራ ይሰራል፡፡

በደም ልገሳ ላይ የሚሰራው የወጣቶች ማህበር ለህብረተሰቡ ደም መለገስ ስላለው ጥቅምና ተያያዥ ጉዳዮች በማስተማርና በማነሳሳት ረገድ አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ይታመናል የሚሉት ዶክተሩ፣ አመቱን ሙሉ ደም የማሰባሰብ ወጥ የሆነ አሰራር ቢኖርም የደም እጥረት እንዲያጋጥም የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡

እንደ እርሳቸው በየቀኑ በርካታ ዩኒት ደም ቢሰበሰብም የተሰበሰበው ደም በምርምራ ሲታይ የተለያዩ በሽታዎች እንዳሉበት ሲረጋገጥ ውድቅ መደረግ፣ እንዲሁም የኔጌቲቭ ደም ለጋሾች ቁጥር ማነስ፣ የድንገተኛ አደጋዎች መጨመር እና ሌሎች ምክንያቶች ለደም እጥረት መከሰት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ማንኛውም ደም ለጋሽ አቅራቢያው ወደሚገኝ የደም ባንክ ደም ለመለገስ ሲመጣ በመጀመሪያ የተለያዩ የጤና መጠይቆች እና ምርመራዎች ይደረጉለታል፤ ደም ለመስጠት ብቁ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ከ450 ሚ.ሊ ያልበለጠ አንድ ከረጢት ደም ይለግሳል።

በጎ ፍቃደኞች ደም ሲለግሱ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ከመታደጋቸው ባለፈ የደም አይነታቸውን ጨምሮ የጉበት፣ የኤች.አይ.ቪ፣ የአባላዘር እና የሌሎች በቫይረስ የሚተላለፉ በሽታዎች ምርመራ ውጤታቸውን አቅራቢያቸው ወደሚገኝ የደም ባንክ ቀርበው ከምክር አገልግሎት ጋር መውሰድ መቻላቸውም ሌላው ተጓዳኝ ጥቅም እንደሆነ አስረድተዋል።

ሁሉም ማህበረሰብ ደም መለገስ ያለውን ጥቅም በመረዳት በሚሰራበት ተቋም፣ በሚኖርበት አካባቢ በቡድንም ሆነ በግሉ በሚመቸውና በሚቀርበው ማዕከል ደም በመለገስ ማህባራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ዶክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ማንም ሰው በደም እጦት መሞት የለበትም የሚል መርህ ያለው ሲሆን፣ ለዚህም ከአንድ አገር አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ቢያንስ 1 በመቶ የሚሆነው ደም በቋሚነት መለገስ ይኖርበታል ይላል። ይሄ ስሌት ደግሞ በእኛ አገር ብቻ እስከ 1 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለጋሾች እንዲኖሩ ያስገድዳል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንድ ግለሰብ ቋሚ የደም ለጋሽ ለመባል በዓመት ቢያንስ 3 ጊዜ ደም መለገስ ይኖርበታል፤ ቢሆንም ግን በኢትዮጵያ ደም የሚለግሱ ሰዎች አሐዝ በየዓመቱ ከ 0 ነጥብ 3 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ነው::

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ያለው የደም ልገሳ ባህል ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ትውልዱ ይህን በመቀየር ለወገን ደራሽነቱን ደም በመለገስ ማሳየት እንደሚጠበቅበትም ዶክተሩ ያስረዳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ስቴድየም አካባቢ በሚገኘው ደም ባንክ ደም ስትለግስ ያገኘናት ወጣት መሰረት አሰፋ ደም መለገስ በሌሎች ህይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ቀላል ተግባር መሆኑን ትናገራለች:: ደም መለገስ በደም እጦት በሞት አፋፍ ላይ ላሉ ህይወት መስጠት ነው የምትለው ወጣቷ፣ ለጋሽ ለመሆን የራስ ተነሳሽነትና ፈቃደኝነት ብቻ በቂ እንደሆነ ነው ያረጋገጠችው።

ወጣት መሰረት ያለ ማንም ጎትጓችነት ደም መለገስ ከጀመረች ቆየት ማለቷን አስታውሳ፣ ደም የሚለግሱ ሰዎች ምንም አይነት የጤና እክል የማይገጥማቸው ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም ለጤናማ ህይወት የሚያበቃ መሆኑን ከራሷ የህይወት ተሞክሮ ተነስታ ተናገራለች፡፡

ደም መለገሰ ከምንም በላይ የህሊና እርካታን እንደሚሰጥ የነገሩን ሌላኛው አስተያየት ሰጪም፣ ለ39ኛ ጊዜ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው አቶ ተስፋሁን ገብረመድህን ናቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ ደም በመለገስ ለወገን ደራሽነታቸውን ማረጋገጥ የጀመሩት አቶ ተስፋሁን፣ ደም መለገስ ለሰጪው ምንም ጉዳት የሌለው ለተቀባዩ ግን ህይወትን መታደግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ደም መለገስ በተለይ ለወላድ እናቶች፣ በከባድ የጤና እክል ለሚሰቃዩ፣ ቀዶ ጥገና ለሚያደርጉ  ወይም  በአደጋ ምክንያት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ያጋጠማቸውን ሰዎችን ህይወት ለመታደግ የሚያስችል በጎ ተግባር በመሆኑ ሲለግሱ ከፍኛ የሆነ የአእምሮ እርካታ እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል፡፡

ደም በመለገስ በሚደረግ ተባባሪነት ውስጥ ተመርምሮ የራስን ጤና ማረጋገጥ ከመቻሉም ሌላ በርካታ የጤና ጥቅሞች ስላሉት እድሜያቸው እስከፈቀደ ድረስ ያለማቋረጥ ለመለገስ ለራሳቸው ቃል መግባታቸውንና ሌሎች ወገኖችም ደም በመለገስ ወገናዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዝነው በጀት አመት እስከ መስከረም 30 በአዲስ አበባ ከተማ 40 ሺህ ዩኒት ደም እና በመላው ኢትዮጵያ ደግሞ በክረምቱ መርሃ ግብር 120 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ከኢትዮጵያ ደምና ህዋስ ባንክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review