ህፃናት እና ተንቀሳቃሽ ስልክ

You are currently viewing ህፃናት እና ተንቀሳቃሽ ስልክ

“ልጄ የስልክ ጥገኛ ከመሆኑ የተነሳ ዘመድ ቤት እንኳን ስወስደው ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ አይጫወትም”

ወላጅ  ወ/ሮ ሳምራዊት ከበደ

ዘመኑ አብዛኛው ነገር በቴክኖሎጂ የሚከናወንበት ሆኗል፡፡ በዚህም ቴክኖሎጂ ከሕይወታችን ጋር ተቆራኝቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሁሉም የእድሜ ክልል ያለ የማህበረሰብ ክፍል ይጠቀመዋል፡፡ በአግባቡ ለተጠቀመበት የገዘፈ ጥቅም አለው፡፡ የህይወትን ውጣ ውረድ ያቃልላል፤ ስራንም ያቀላጥፋል፡፡ በተቃራኒው ከሆነ  ደግሞ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡

“ሞባይል እና እጄ ባይነጣጠሉ ደስ ይለኛል፡፡ አባቴ ስልኩን ለስራ ፈልጎት ሲወስድብኝ በእናቴ ስልክ እጠቀማለሁ” በማለት ለስልክ ያላትን ፍቅር የገለጸችልን የ14ዓመቷ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሙኒራ ያሲን ናት፡፡

ለትምህርቴ አጋዥ የሆኑ ነገሮችን እያወረድኩ አነብበታለሁ፡፡ የማላውቃቸውን አዳዲስ ነገሮችንም እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ ነገር ግን ጨዋታ (ጌም) መጫወት እና ቲክቶክ መከታተል በጣም ስለምወድ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው እነዚህን በማየት ነው፡፡ ከትምህርት ይልቅ ትኩረቴ በሚያዝናኑ ነገሮች ላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም እስከ ስድስተኛ ክፍል ከ2ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ነበር የምወጣው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ደረጃዬ ግን ቀንሷል ስትልም የስልክ ጥገኛ መሆኗ በመደበኛ የትምህርት ውጤቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረባት ገልፃለች፡፡

ቤተሰቦቼ የሚመስላቸው በስልኬ የማነብብ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ከማንበብ ይልቅ ጌም መጫወት እመርጥ ነበር፡፡ አሁን አሁን እየገባኝ ሲመጣ የውጤቴ ማሽቆልቆል ምክንያቱ ጊዜዬን ስልክ ላይ ማሳለፌ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በደረጃ የምበልጣቸው ተማሪዎች ሲበልጡኝ በጣም ያናድዳል፡፡ ቤተሰቦቼም ይህንን በመረዳት ከስልክ ይልቅ መጽሐፍ ገዝተውልኛል፡፡ እያነበብኩ ነው፡፡

 “በየግላቸው ስልክ ያላቸው ጓደኞቼ መልዕክቶችንና ፎቶቸውን ይላላካሉ፡፡ በእኔ እድሜ እና ከእኔም በታች ያሉ ተማሪዎች ትኩረታችን መሆን ያለበት ትምህርት ላይ ነው። ሌሎች ነገሮች ጨዋታም ይሁን ፊልም ማየት የትምህርት ጊዜን በማይነካ መንገድ መሆን አለበት” ስትልም ሙኒራ  ጊዜዋን ለትምህርቷ ብቻ እንደምታውለው ተናግራለች፡፡ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ህልሜ ነው ትላለች፡፡

ሌላኛዋ አስተያየታቸውን የሰጡን ወይዘሮ ሳምራዊት ከበደ የሶስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ በተቻላቸው መጠን ልጆቻቸውን በስርዓትና በስነ ምግባር አንፀው ለማሳደግ ይጥራሉ፡፡ ቢሆንም የሞባይል መተግበሪያዎች ሰዎች ጊዜያቸውን በእሱ ላይ ብቻ እንዲያሳልፉ ለማድረግ ታስበው የተሰሩ እስከሚመስል ድረስ ልጃቸው ውሎው ከስልክ ጋር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የመጀመሪያ ልጃቸው ከምግብ ይልቅ ስልክን ምርጫው ያደርጋል፤ ምግብ እንዲበላ ሲጠየቅም በአንድ እጁ ስልክ በአንድ እጁ ደግሞ ምግብ ይዞ ነው የሚመገበው፡፡ ቲክቶክ፣ ጌሞች እና ፊልም ያያል ሲሉ የስልክ ጥገኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

“ቴክኖሎጂ በ2016 የትምህርት ዘመን ልጄን በትምህርቱ ዝቅተኛ ውጤት እንዲያስመዘግብም አድርጎታል፡፡ ከዚህ በፊት በራሱ የቤት ስራ ይሰራ ነበር፡፡ በወቅቱ ጥያቄዎችን በሚሰራ የስልክ መተግበሪያ ነበር ሰርቶ የሚሄደው፡፡ መምህሮቹም ክፍል ውስጥ ያደርግ በነበረው የነቃ ተሳትፎ የደረጃ ተማሪ መሆን ነበረበት ብለውኛል። እኔም ቤት ውስጥ የተማረውን አለማንበቡ ለውጤቱ ዝቅ ማለት ምክንያት እንደሆነው ተረድቻለሁ። መተግበሪያው የእኔን ልጅ ብቻ ሳይሆን መሰል ተማሪዎችም በራሳቸው እውቀት እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል” ሲሉ በልጃቸው ውጤት ማሽቆልቆል የተሰማቸውን በብስጭት ነግረውናል፡፡

ልጄ የስልክ ጥገኛ ከመሆኑ የተነሳ ዘመድ ቤት እንኳን ስወስደው ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ አይጫወትም፡፡ ከቤተሰብ ጋርም ያለው ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ ነው፤ ለሌሎች ስሜት ደንታ የለውም፡፡ እድሜውን የማይመጥኑ አላስፈላጊ ምስሎችና ጽሑፎችን ሊያይና መንገዱን ሊስትብኝ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ የሚሉት ወይዘሮዋ፣ የወደፊት እጣ ፈንታው እንደሚያስጨንቃቸው አብራርተዋል፡፡ 

ወይዘሮዋ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን የምክር አገልግሎት የመስጠት፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ተገቢውን ቅጣት የመቅጣት፣ የስልካቸውን ምስጢር ቁልፍ በመቀየር ለመከልከል ቢሞክሩም ምንም አይነት ለውጥ እንዳላመጡ ነው የገለፁት።

ልጆች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ረገድ የተካኑና የተለያዩ ጥቅሞችንም የሚያገኙበት ቢሆንም በአግባቡ እንዲጠቀሙ ክትትል ካላደረግንላቸው ጉዳቱ ያመዝናል። ልጆች ስልክን የሚጠቀሙት እንዴት ነው? የትኞቹን ገጸ ድሮች ከፍተው ያያሉ፣ የትኛውን ጨዋታ ይጫወታሉ? ስልካችንን በመጠቀም ምን ያህል ጊዜ ያሳልፋሉ? የሚለውን ጠንቅቆ ማወቅ፣  ብስለታቸውንና ራስን የመግዛት ችሎታቸውን መገምገም አስፈላጊ መሆኑን ከራሳቸው ልጅ በመነሳት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪያችን አቶ ሃይሉ ይድነቃቸው ይባላሉ፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ልጆቻችን በስነ ምግባር ለመታነጻቸውም ሆነ ከዚህ  ተቃራኒ መሆን ትልቁን ድርሻ የምንጫወተው ወላጆች ነን። ልጆችን ማሳደግ ማለት መሠረታዊ  ፍላጎታቸውን ማሟላት ብቻ ሳይሆን ከቴክኖሎጂ ጋር  ያላቸውንም ግንኙነት መከታተል  ተገቢ ነው፡፡

ልጆች ማለት የምናደርገውን ሁሉ ለማድረግ የሚሞክሩ፤ ያዩት ነገር ሁሉ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ እንዳይረብሹ በሚል፣ ምግብ አልመገብም ሲሉ ስልክ በመስጠት ለመደለል እንሞክራለን። ነገር ግን ይህ ሂደት በአግባቡ ካልሆነ ከልጆቹ ይልቅ ዳፋው ለእኛ ነው የሚተርፈው፡፡ ለምሳሌ፡- ሁለተኛ ልጄ ብዙ ጊዜ ከምታለቅስ በሚል ስልክ ይሰጣታል፡፡ ይህ ሂደት ልምድ ሆኖ ቀጠለ፡፡ አምስተኛ ዓመቷ ላይ አይኗ እንባ እያነባ ሲያስቸግራት ህክምና ወሰድኳት። የምርምራ ውጤቱም አይኗን እንዳመማት ነገሩኝ። ለጊዜው ለህመሙ መድሃኒት ያዘዙላት ቢሆንም፤ አይኗ አደጋ ላይ እንዳለ ነው ያሳሰቡን፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከስልክ ጋር ያላትን ቁርኝት እንዲቀንስ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የጥንቃቄ ርምጃዎችን እንድታደርግ እያደረግን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሃይሉ በመልዕክታቸው፤ ልጆቻችንን ስለምንወድዳቸው ወይም ስላስቸገሩን የፈለጉትን ነገር ሁሉ ስናደርግላቸው የሚያመጣባቸውን ጉዳትም ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ስልክ እንዲያይ የፈቀድንለት ልጅ ሁልጊዜ ግንኙነቱ የሚሆነው ከስልኩ ጋር ብቻ ነው፡፡ ይህም ከቤተሰብ ጋር ያለውን ፍቅር ይቀንሳል፤ አልፎ ተርፎም በልጆች ደረጃ መታየት የሌለባቸውን ነገሮች በማየት ወዳልተፈለገ መንገድም ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አግባብነት የሌለው የቴክኖሎጂ (የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች) አጠቃቀም በልጆች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀዳማይ ልጅነት እድገት እንክብካቤ የሁለተኛ ዓመት የፒኤች ዲግሪ ተማሪ እና ሁለንተናዊ (አካላዊና ስነ ልቦናዊ) የህፃናት እድገት  ባለሙያ ወይዘሮ ጆርጎ ድሪባ  ናቸው፡፡ ጊዜው የቴክኖሎጂ  እንደመሆኑ መጠን ልጆች በቀላሉ እውቀት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በአግባቡ ከተጠቀምንበት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ወላጆች ስልክን ለልጆች የሚሰጡት ሲያለቅሱ ለማባበል፣ እረፍት ተሰምቷቸው ተረጋግተው እንዲቀመጡ እንዲሁም ምግብ እንዲመገቡ በሚል ነው። ይህ ሲሆን ጥቅማቸውን እንጂ ጉዳታቸውን አናስተውልም፡፡ ልጆች ረዘም ላለ ጊዜ ከስልክ ጋር ሲቆዩ የልጆች የመፍጠር፣ የመመራመር፣ የማሰላሰል አቅማቸው እንዲዳከም፣ የቋንቋ ችሎታቸው እንዳይዳብርና ከሰዎች ጋር መግባባት እንዳይችሉ  ያደርጋቸዋል፡፡

በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያቅፉበትና የሚስማሙበትን እንዲሁም አብረው የሚጫወቱበትን፣ ፍላጎታቸውን የሚያዳምጡበት ጊዜ ስለሚያሳጣ ልጆችና ወላጆች እንዳይተዋወቁ፣ ከእህት ከወንድም እንዲሁም ከጎረቤት ልጆች ጋርም የሚኖራቸው ግንኙነት እንዲቀንስ  ያደርጋል። ወላጆች የሚያዩትን ነገር ስለማይመርጡላቸው ከባህላችን፣ ከእምነታችን ያፈነገጡና ላልተገቡ የልጆችን ስብዕና ለሚጎዱ ድርጊቶች እንዲጋለጡም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በትምህርታቸውም ላይ የሚያሳድረው ጫና እንዲሁ በቀላል የሚታይ አይደለም። ትኩረታቸውን ሰብስበው ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉና ውጤታማ እንዳይሆኑ እስከማድረግም ይደርሳል ብለዋል፡፡

“ማህበራዊ መስተጋብር የሚታወቀው በመኖር ነው” የሚሉት ባለሙያዋ፤ ልጆች አካባቢን ማየት፣ ማጤን፣ ከጓደኞቻቸው ጋር መጫወት፣ መጣላትና መታረቅ እንዲሁም ከሰው ጋር እንዴት እንደሚኖሩ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ ውሏቸው ከስልክ ጋር ሲሆን ግን እድሜያቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ከሰው ጋር ለመኖር እንዲቸገሩና በስነ ልቦናም የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ 

ስልክ እየነካኩ፣ ፊልሞችን እያዩ የሚያድጉ ልጆች መጻሕፍት እያነበቡ እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር እየተጫወቱ ካደጉት ጋር ሲነፃፀሩ ሁሉንም ነገር ወዲያውኑ እንዲሆን የመፈለግ ፀባይ ይላበሳሉ። ይህም ትምህርትን ቁጭ ብሎ ለማጥናት፣ አንድን ሃሳብ ለረጅም ጊዜ በጥልቀት ለማሰላሰል እንዳይችሉ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ነሐሴ 2021 Australian Institute of Family studies በተሰኘ ድርጅት “Too much time on screens? Screen time effects and guidelines for children and young people” በሚል ርዕስ በአንጋ ጆሺ እና ትሪኒ ሂንክለይ የተጠናው ጥናትን ባለሙያዋ ጠቅሰው እንደገለፁት፤ ልጆች ከተወለዱ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመታቸው ስልክ እና ቴሌቪዥንን ጨምሮ ምንም አይነት ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ማየት የለባቸውም፡፡

እስከ 5 ዓመት ያሉ ልጆች ደግሞ የተመረጡ ይዘቶችን በቀን ለ1፡00 ሰዓት ያህል ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው እና ሌሎችም እንደ ዕድሜ ደረጃቸው የሚያዩበት ጊዜ መወሰን የሚመከር እንደሆነ ነው ባለሙያዋ የተናገሩት፡፡

“ልጆች ወላጆችን ነው የሚመስሉት” የሚሉት ባለሙያዋ፤ “ልጃቸውን ስልክ አትንካ? ይሄንን አትይ? ከማለታቸው በፊት ቅድሚያ እነሱ ምን ያህል ስልካቸው ላይ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ለይተው ማወቅ አለባቸው፡፡ ከዚህ በመነሳትም እናትና አባት ወይም አሳዳጊዎች ቁጭ ብለው በመመካከር ‘ልጆቻችን ምንድን ነው ማየት ወይም ደግሞ ማንበብ ያለባቸው?’ የሚለውን በመምረጥ እንዲያዩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ወላጆች ለልጆቻቸው ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ልጆችን ቀርቦ ፍላጎታቸውን ማወቅ፣ የሚፈልጉትን ነገር እንዲያዩ ማድረግ እንዲሁም የማይመጥናቸውን ነገር ደግሞ እንዳያደርጉ መከልከል ከወላጆች እንደሚጠበቅም አክለዋል።

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review