AMN-ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ271 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን ዳንኤል፤ በ2017 በጀት ዓመት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመሰብሰብ መታቀዱን አውስተዋል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቦንድ ሽያጭ፣ በ8100 አጭር የፅሑፍ መልዕክትና በስጦታ ከ271 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በዓመቱ የታቀደውን ድጋፍ ለማሰባሰብ በትኩረት ይሰራል ያሉት ስራ አስፈጻሚው፤ ህዝቡም እስከ ግንባታው ፍጻሜ ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መገናኛ ብዙሃንና እውቅ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን ለህብረተሰቡ በማሳወቅ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የታላቁ ህዳሴ ግድብን 3ኛ እና 4ኛ ተርባይኖችን ሥራ መጀመራቸውን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወንዙ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም በተጨማሪ የግድቡ የውኃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜትር ኪዩብ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ ጀምረዋል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ፍሰትን በመቆጣጠር፣ የጎርፍ አደጋ ሥጋትን በመቀነስ፣ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውኃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።