ለህፃናት ደስታ፤ ለወላጆች እፎይታ – Copy

You are currently viewing ለህፃናት ደስታ፤ ለወላጆች እፎይታ – Copy

በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ የሒሰብ ክፍል ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ የሺወርቅ ታደለ ልጃቸውን በተቋሙ በሚገኘው የህፃናት ማቆያ በማስቀመጥ ሥራቸውን ካለምንም ስጋት ይከውናሉ፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየትም ማቆያው ሙሉ ለሙሉ ቀልባቸውን በመሰብሰብ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ትልቅ እገዛ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል፡፡ የ11 ወር ልጃቸውን በማቆያው ማስቀመጥ ከጀመሩ አምስት ወር እንደሆናቸውና ከወጪ በተጨማሪም ʻእንዴት ሆኖ ይሆን?’ ከሚል ስጋት እንደታደጋቸውም አክለዋል፡፡ 

የሦስት ዓመት ልጃቸውን በህፃናት ማቆያው በማስቀመጥ ሥራቸውን እየሠሩ የሚገኙት ሌላኛዋ ወላጅ ወይዘሮ ፀሐይ አህመድ ናቸው፡፡ ለሰልጣኞች መስጠት ያለባቸውን ትምህርት በአግባቡ መስጠት ለመቻላቸው ዋነኛው ምክንያት ልጃቸውን ካለምንም ስጋት በቅርበት መከታተላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። “የህፃናት ማቆያው ለኔ ብዙ ነገሬን ሞልቶልኛል፡፡ የሥራ ሰዓቴን በአግባቡ እንድጠቀም አድርጎኛል፡፡ በተለይም ‘ልጄ ምን ሆነ?’ ብዬ ሥራዬን ትቼ ከመሄድ እዚሁ አጠገቤ ሆኖ ማየቴ ለኔ እረፍት ይሰጠኛል፡፡ ከዚህ ቀደምም የመጀመሪያ ልጄን በዚሁ የህፃናት ማቆያ በማስቀመጥ ተጠቃሚ ሆኛለሁ” በማለት ከማቆያው የተጠቀሙትን አብራርተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ፀሐይ ገለጻ፣ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር አብሮ ሲጫወት በመዋሉ ልጃቸው ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ህጻኑ እነዚህን ሁሉ ጥቅሞች ማግኘቱ አካላዊና አእምሯኣዊ እድገቱ ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያመጣ ያግዘዋል፡፡ ልጆች ታዝለው የሚውሉ ከሆነ ለእድገታቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡ ሰውነታቸው ይተሳሰራል። ዛሬ ላይ ልጃቸው ፈጣንና ሳቂታ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እሳቸው ስራቸውን ሳይቸገሩ ለማከናወን ችለዋል፤ ድካማቸውንም አቃልሎላቸዋል፡፡ እንዲህ አይነት ለራሳቸውም ሆነ ለልጃቸው ምቹ ሁኔታ ለፈጠረላቸው መንግስትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ 

አቶ ዘሪሁን አባተ በኮሌጁ የህንፃ አስተዳደር አገልግሎት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የኮሌጁን የህጻናት ማቆያ አመሰራረትና አገልግሎት አስመልክተው እንደገለጹት፤ የተመሰረተው በ2009 ዓ.ም. ክረምት ላይ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ የገባው ደግሞ 2010 ዓ.ም ነው። በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጄንሲ የአሁኑ ስራና ክህሎት ቢሮ ለ3 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ማለትም ለጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ለተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ  እና ለእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የህጻናት ማቆያ ባመቻቸው ዕድል  ቢሮው 2 ሞግዚቶችን ቀጥሮ በሙከራ ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት በማሰብ ወደ ስራ ሊገባ ችሏል፡፡

የኮሌጁ ሴት አሰልጣኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች ልጆች እንዲሁም የተቸገሩ የህጻን አባት የሆኑ ሰራተኞች ጭምር በማቆያው የዕድሉ ተጠቃሚዎች ናቸው። ማቆያው ከሰው ሃብት አንጻር አሁን ላይ 4 ተንከባካቢዎች እና 1 የጽዳት ባለሙያ ያለው ሲሆን፤ ከ6 ወር እስከ 4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 26 ህፃናት ይገኛሉ፡፡ ለህፃናቱ የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ መጫዎቻዎችን የማሟላት ስራ የተሰራ ሲሆን ዕድሚያቸው ከፍ ላሉ ህፃናት ደግሞ በኮሌጁ የእንጨት እና የብረት ስራ ማኑፋክቸሪንግ ዲፓርትመንቶች አማካኝነት ዥዋዥዌ፣ መንሸራተቻና መሽከርከሪያ ግብዓቶች በዘመናዊ መልኩ ተሰርተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል ብለዋል፡፡

ማቆያው አሁን ላይ የመጫወቻ፣ የመኝታ፣ የመፀዳጃ እንዲሁም የምግብ ማብሰያ ክፍሎች አሉት። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶች በውስጡ ይገኛሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ሴት ሰራተኞች ስራቸውን በአግባቡ ለመስራት ከሚቸገሩባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ህጻናት ልጆቻቸውን በስራ ሰዓት የሚንከባክብላቸው አልያም የሚያቆይላቸው አካል አለመኖሩ ነው። በተለይ ደግሞ የሚንከባከብ የቅርብ ቤተሰብ የሌላቸው ወይም ሰራተኛ ለመቅጠር ዝቅተኛ የሆነ ገቢ ያላቸው እናቶች ላይ ችግሩ ጎልቶ ይታያል። በአንድ በኩል ሰራተኛ እንኳ ቢኖር እናት ልጇን ለማጥባትና ለመከታተል የስራ ቦታዋ የራቀ ከሆነ ሃሳቧም ስለሚከፈል በስራዋ ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ትቸገራለች። ስለሆነም የህጻናት ማቆያ እናቶች በሚሰሩበት ተቋም መኖሩ ለእናቶች እፎይታን እንደሚፈጥር መገመት ቀላል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮሌጁ የህጻናት ማቆያ ሞግዚት የሆኑት ጌጤ ቦጋለ የሚናገሩትም ከላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። ሞግዚቷ በማብራሪያቸው፤ ህፃናትን መንከባከብ አስደሳች ተግባር ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ እናቶች ልጆቻቸውን በቅርብ ሆነው መከታተላቸው ለአእምሮ እረፍትን ይሰጣቸዋል፤ በስራ ገበታቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለይም የሚያጠቡ እናቶች ከወሊድ በኋላ የእረፍት ጊዜያቸው ቢያልቅ እንኳ ለልጃቸው ያደርጉት የነበረውን እንክብካቤ እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በቀጣይ የህፃናት ማቆያውን አስፍቶ እና በበለጠ መንገድ ምቹ አድርጎ ለመስራት ትልቅ እቅድ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ዘሪሁን ወላጆች ካለምንም ስጋት እና መሳቀቅ ስራቸውን በአግባቡ ለመከወን እንዲችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review