ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- ባለሙያ

You are currently viewing ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- ባለሙያ

AMN – ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

ሰሞኑን እየተስተዋለ የሚገኘውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የመሬት መንቀጥቀጥ የምህንድስና ባለሙያው ዶክተር መሰለ ሀይሌ ገለጹ፡፡

የመሬት መንቀጥቀጥ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣በመሬት ንጣፍ ላይ የአለቶች መውደቅ እና በከርሰ ምድር ውስጥ በሚፈጠር ፍንዳታ በአነስተኛ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዋናነት ርዕደ መሬት ከምድር በታች በሚገኙ አለታማ ቁሶች ግጭት የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ክስተትም ነው።

ሰሞኑን በአፋር ክልል ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ በመዲናችን አዲስ አበባም የመሬት ንዝረት ተሰምቷል፡፡

ይህንን ተከትሎ ከ ኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የመሬት መንቀጥቀጥ የምህንድስና ባለሙያው ዶክተር መሰለ ሀይሌ በኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመት ውስጥ 12 የመሬት መንቀጥቀጦች መድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡ከሰሞኑ የታየውም ብዙ ጉዳት የሚያስከትል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ ግንባታዎች አደጋን መቋቋም የመቻል መጠናቸው አናሳ መሆኑ እና የሰዎች የጥንቃቄ ጉድለት አደጋውን ሊያባብስ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዜጎቿን ደህንነት ለመጠበቅ አላማ ያደረገ የህንፃ አሰራር ህግን የደነገገች ሀገር ብትሆንም ከመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ አደጋዎች አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ባለሙያው አንስተዋል፡፡

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው የመሬት ንዝረት አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል በግንዛቤ እጥረት የሚወሰደው እርምጃ ተገቢ ያልሆነ ስለመሆኑ በማንሳት መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው ከህንጻ ለመውረድ ከመሞከር ይልቅ ባሉበት ሆኖ በር ስር መቆም፣ ጠረጴዛ እና አልጋ ስር መግባትን መደረግ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል ጠቅሰዋል፡፡

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review