ለምክክሩ ስኬት  የፓርቲዎቹ  የተግባር  ምላሽ እንዴት  ይገለጻል? 

“በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም” የሚለው ሀገራዊ ብሂል ለተለያዩ ጉዳዮች የሚጠቀስና  ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ነው፡፡ ከሀገራዊ ሁኔታ ጋር ስናያይዘው የችግሮቻችንን ስር መሰረት በደንብ ማወቅ ካልተቻለ እንዲመጣ የምንመኘውን ዘላቂ ሰላም፣ አስተማማኝ ልማትና ዴሞክራሲን ባህል የማድረግ ጉዳይ በቀላሉ ማረጋገጥ አይቻልም። የችግሮቻችንን ወይም ህመሞቻችንን መነሻ ምክንያቶችን መለየት ማለት ለመፍትሔ ፍለጋው ግማሽ መንገድ መሄድ ማለት መሆኑን ያመላክታል። በህክምና ሙያ ሀኪሞች እንደሚሉት አንድ ታማሚን ከህመሙ ለማዳን ታማሚው ስለህመሙ ምልክቶችና ስለሚሰማው ስሜት የሚሰጣቸው መረጃዎች በጣም ጠቃሚና ወሳኝ ግብዓት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መጋቢት 14 ቀን በ2014 ዓ.ም በአዋጅ ሲቋቋም በሀገራችን ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ በመለየት፣ በተለዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጎ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት በማለም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ ከትግራይና አማራ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን እያገባደደ ይገኛል። በኦሮሚያ ክልልም የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ከታህሳስ 7 ቀን እስከ ታህሳስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር መድረኩ ሲካሄድ ከመነሻው ጀምሮ እያንዳንዱ ሂደት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያሳተፈ፣ አካታችና አሳታፊነት በተሞላበት አግባብ እንዲከናወን ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የሚረጋገጠውና ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ በቀናነት (genuine) እና በስፋት ሲሳተፍ ነው፡፡

በምክክሩ ከሚሳተፉና ቁልፍ ሚና ካላቸው አካላት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ይጠቀሳሉ፡፡ የጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ዓይነት ተሳትፎ እያደረጉ ነው? ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል? ስንል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር  አነጋግሯል፡፡

በምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ

በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው ሰላምና ልማትን ለማምጣት፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለበርካታ ዓመታት ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አስተዳደር ሀሳቡ ሲነሳ ማነው የተጣላው? ማን ከማን ይታረቃል? በሚል ጥያቄውን ውድቅ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ተነሳሽነቱን በመውሰድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም በማድረግ ወደ ስራ መገባቱ መልካም የሚባል እርምጃ እንደሆነ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ደስታ ዲንቃ ተናግረዋል፡፡

አገራት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ያሉት በምክክር፣ በውይይት፣ በድርድር፣ በሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ በዓለም ላይ የፖለቲካ ጥያቄዎች የተቃኙትና መፍትሔ ያገኙት በውይይት ነው፡፡ አሜሪካ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ሆና ልትመሰረትና ሀያል ልትሆን የቻለችው ከነበሩ ከ50 በላይ መንግስታት ውስጥ በ13ቱ የተጀመረ ውይይት ወደ ሁሉም ሰፍቶ መግባባት ላይ በመድረስ እንደሆነ ዋና ፀሐፊ ያነሳሉ፡፡

አቶ ደስታ እንደገለፁት፣ በ2010 ዓ.ም የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች እርስ በርስ ለመመካከርና ለመነጋገር የቃል ኪዳን ሰነድ እንዲፈርሙ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲመሰረት ዕድል ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 70 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት አቅፎ በመያዝ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ከእነዚህም አብዛኞቹ ከኮሚሽኑ ጋር ተባብረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ ከኮሚሽኑ አመሰራረትና የኮሚሽነሮቹ አመራረጥ ላይ ጥያቄ በማንሳት የማይሳተፉ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን፤ በጊዜ ሂደት ሀሳባቸውን በመቀየር በምክክሩ ላይ የሚሳተፉት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተሳታፊ ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከሰባት አይበልጥም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ የተመሰረተበት ሂደት፣ ገለልተኝነትና አካታችነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ እንደሆኑ አቶ ደስታ ያነሳሉ፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማም ያየን እንደሆነ በአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ታቅፈው ከሚንቀሳቀሱ 18 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 16ቱ የምክክሩን ሂደት በመደገፍ በሂደቱ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ የተሳታፊዎች ልየታ ሲከናወን የጋራ ምክር ቤቱ በ119 ወረዳዎች በተባባሪነት ተሳትፎ አድርጓል። አባል የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምክክር አጀንዳ በመስጠት ተሳትፈዋል። የተለዩ አጀንዳዎች ወሳኝ በመሆናቸው በእነዚያ ላይ ተወያይቶ መግባባት ላይ መድረስ ከተቻለ የሀገሪቱን ችግር ይቀረፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት በምክክሩ የሚሳተፉ ወገኖች “ምክክሩ ውጤት ያመጣል” የሚል ሙሉ እምነት በመያዝ መሳተፍ አለባቸው። በዚህ ረገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ሂደት ለመሳተፍ ሲወስኑ ሀገሪቱ ያለችበትን ችግር ከግምት በማስገባት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሆነ አቶ ደስታ ያነሳሉ፡፡  በምክክሩ ሂደትም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር አጀንዳ የሚሰጡ ተሳታፊዎችን በመለየት፣ አንድ ተባባሪ አካል ሆኖ ከፌዴራል እስከ ዞን ድረስ ባሉት መዋቅር ኮሚሽኑን በመደገፍ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ የተሳታፊዎች ልየታ አካታች እንዲሆን ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡ በሂደቱ ችግር ሲያጋጥም እንዲታረም ለኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡

አቶ ደስታ እንደገለፁት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ኮሚሽኑ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ከጎኑ በመሆን እየደገፈው ይገኛል። የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአጀንዳ ሀሳብ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንደ የጋራ ምክር ቤትም  የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማወያየት የአጀንዳ ሀሳብ ተዘጋጅቶ ለኮሚሽኑ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል “ምክክሩ ተጀምሯል” ማለት ነው የሚቻለው። ለአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን እያንሸራሸሩ ይገኛሉ፡፡

በምክክሩ እየተሳተፉ የማይገኙ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክሩ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ በሚዘጋጅበት ወቅት ጎን ለጎን የሀገራዊ ምክክር ጉዳይ ላይ ኮሚሽነሮች ተገኝተው ገለፃ እንዲያደርጉ ተደርጓል። በዚህም መልሰው ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑት እድል ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ፦ በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ መካከል በባህር በር ተጠቃሚነት ዙሪያ በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ውይይት ሲደረግ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተገኝተው በምክክሩ ሂደትና እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ገለፃ እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

ኮሚሽኑ ምን ይላል?

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያልተሳተፈበት ምክክር ውጤታማ ስለማይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ በሰፊው እንዲሳተፉ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለሀገራዊ  ምክክር መድረኩ መሳካት ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ከተለዩ አካላት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኞቹ እንደሆኑ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ይናገራሉ፡፡ የአጀንዳ ማሰባሰብ በተከናወነባቸው የተለያዩ ክልሎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአጀንዳ ሀሳብ የሚሰጡ ተሳታፊዎችን በመለየት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ኮሚሽነር ሙሉጌታ እንደገለፁት፣ ኮሚሽኑ ስራውን እንደጀመረ አካባቢ በምክክር ኮሚሽኑ ላይ ጥያቄ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች “አንሳተፍም” በሚል ከሂደቱ እራሳቸውን አግልለው ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውይይቶችና ምክክሮች፣ ኮሚሽኑ በሚሰራቸው ስራዎች አመኔታ እያሳደጉና ሂደቱን ወደ መደገፍ መጥተው አብረው በመስራት ሚናቸውን በመወጣት ላይ ናቸው፡፡ በኮሚሽኑ ከገለልተኝነት ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ትክክለኛ ያልሆነ አስተያየት ማረጋገጥ የቻሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡

ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ግጭት ለመግባት መንስኤ የሆኑ መሰረታዊ ችግሮች ምን እንደሆኑ ለይተው አጀንዳ መስጠትና ኮሚሽኑ ስራውን በምን መንገድ እያከናወነ እንደሆነ መታዘብ የሚችሉበት ዕድልም ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኞቹ የምክክሩን ሂደቱን በመደገፍ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር አብረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በምክክሩ ሂደት እየተሳተፉ የማይገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምክክሩ እንዲገቡ ከማድረግ አንጻር በተለያዩ ጊዜያት መድረኮችን በማዘጋጀት ውይይት ተደርጓል፡፡ ፓርቲዎቹ በኮሚሽኑ ስራ ላይ ጥያቄ ካላቸው ኮሚሽኑ ለመነጋገር ፈቃደኛ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን እንደ ተባባሪ አካል ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት ተባብሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ የአጀንዳ ሀሳብ የሚያቀብሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተሳታፊዎችን በመለየትና አጀንዳ በመስጠት እየተሳተፈ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎችም በግልና በጋራ አጀንዳ እየሰጡ ይገኛሉ። ኮሚሽኑም በየጊዜው መድረኮችን አመቻችቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ በምክክሩ ዙሪያ ያላቸውን ሀሳብ በመውሰድ እንደ ግብዓት በመጠቀም እየተሰራ ነው፡፡ ብዙዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ ስለምክክሩ ግንዛቤ በመፍጠር እየሰራ ያለው ስራ መልካም እንደሆነ ምስክርነት እየሰጡ እንደሆነ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አንስተዋል፡፡

ቀጣይ ምን ይጠበቃል?

ህዝብ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መለወጥ ካልቻለ እንደ ሀገር የመቀጠላችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ምክክሩ ሀገርን የመታደግ ጉዳይ ስለሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች “በሀገር ጉዳይ ላይ አይመለከተንም” ማለት አይችሉም፡፡ ስልጣን ለመያዝ መፎካከር፣ መንግስትም ሆነ ሀገርን መምራት የሚችሉት ሀገር ሲኖር ነው፡፡ ምክክሩ ሀገርን የማስቀጠል፣ ሰላምን የማረጋገጥ፣ ዜጎችን በሀገራቸው ጉዳይ በ“ያገባናል” ስሜት በባለቤትነት የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠር በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንደሚጠበቅባቸው ኮሚሽነር ሙሉጌታ አንስተዋል፡፡

ከአንዳንድ አካባቢዎች “ግጭት አለ፤ ኮሚሽኑ ምን እየሰራ ነው?” የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ ይህ ጥያቄ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነት ካለመረዳት የሚመነጭ የሚሉት ኮሚሽነር ሙሉጌታ፣ ኮሚሽኑ ዋነኛ ስራው ለአለመግባባትና ግጭት መንስኤ የሆኑ ችግሮች ተለይተውና ውይይት ተደርጎ መፍትሔ እንዲገኝ ማመቻቸት ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ሙሉጌታ እንደጠቆሙት፣ እስከአሁን ባለው ሂደት ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ በቀጣይም የአጀንዳ ሀሳብ በማዋጣትና በምክክሩ ላይ ሀሳብ በመስጠት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። አካታችነትና አሳታፊነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ካለ ጠጋ ብሎ የኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴ መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህ ባለፈ ምክክር ለማድረግ የሰላም መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላም የሚመጣው ደግሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ ከሁሉም በላይ መመካከር መልካም መሆኑን በመረዳት ህብረተሰቡ ልጆቹን በመምከር፣ ሰላምን የሚያደፈርሱትን ወደኋላ በማለትና ሰላማዊ መንገድን እንዲመርጡ በማሳየት መስራት ይጠበቃል። ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በተመለከተም፤ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ እያቀረበ ነው፡፡ አሁንም የእነሱን አጀንዳ ለመቀበል ዝግጁ ሆኖ እየተጠባበቀ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ እነዚህ አካላት በምክክሩ እንዴት ይሳተፉ? የሚለው ላይም ከመንግስት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሙሉጌታ አስፋው በበኩላቸው፤ በሀገራችን መሰረታዊ በሆኑ የማያግባቡ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ ከግጭትና ጦርነት ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር ዋነኛው መውጫ መንገድ ነው፡፡  

ከዚህ አኳያ ምክክሩ የማይመለከተው አካል ስለማይኖር፣ “የሀገር ጉዳይ ያገባናል” የሚል ሁሉም ባለድርሻ አካል የውይይት ርዕሰ ጉዳዮችን በመያዝ ወደ ምክክር ጠረጴዛው መምጣት ይኖርበታል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክሩ ዋነኛ ባለድርሻ አካል፣ ለምክክሩ ውጤታማነት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክር መድረኩ ለውይይት መሆን አለበት የሚሉትን አጀንዳ ወደ ጠረጴዛው ማቅረብና በምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ባላፈ በምክክሩ ሂደት “አንሳተፍም” እና “አልተወከልንም” የሚሉትን በማሳመን ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ማድረግ እንዳለባቸው የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ እስከአሁን በሰራቸው ስራዎች በአንፃራዊነት አመኔታ እየገነባ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ በቀጣይ ገለልተኛነቱን አስጠብቆ በማስቀጠል መሬት ላይ የወረዱ ስራዎችን መስራት አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚያሳድጉ ስራዎችን በመስራት ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review