በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተጀመረው የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ዛሬ ላይ ከ200 በላይ አገራት በዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፊዴሬሽን ታቅፈው ውድድሮችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ከተወዳጅ ስፖርቶች መካከል የሚጠቀሰ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈረንጆቹ 1926 በተመሰረተው ዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የሚተዳደር ነው፡፡ እስከ 40 ሚሊዮን የጠረጴዛ ቴኒስ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችም ስለመኖራቸው የድርጅቱ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በአህጉረ አፍሪካም የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ከ62 ዓመት በፊት የጀመረና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ በእስከ አሁኑ ውጤትም ግብጽና ናይጄሪያ የበላይነት እንዳላቸው ከአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ ከጥቅምት 2 እስከ 9 የሚቆየው የ2024ቱ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮናም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በመሆኑም በዚህ አምድ በውድድሩ ላይ እነማን ይሳተፋሉ? ኢትዮጵያስ ምን አይነት ዝግጅት አድርጋለች? በስፖርቱስ ያላት ውጤታማነት ምን ይመስላል? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን እንቃኛለን፡፡
በአፍሪካ ደረጃ በተለይም የሰሜን አፍሪካ አገራት በጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት የተሻለ ውጤት ያላቸው ሲሆን፣ በዚህም እንደ ግብጽ፣ ቱኒዚያ እንደዚሁም ከምዕራብ አፍሪካ እንደ ናይጄሪያ ያሉ አገራት በውጤታማነታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ለጠረጴዛ ቴኒስ የሚሆኑ በቂ የስልጠናና የመወዳደሪያ ስፍራዎች መኖር፣ በአዳጊዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸውና በርከት ያሉ የአገር ውስጥ ውድድሮች መኖር ለስኬታማነታቸው የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ያላት አፈጻጸም ገና ብዙ የሚቀረው ስለመሆኑ ፌዴሬሽኑ ይገልጻል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር 1980ዎቹ ለጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ወርቃማ ጊዜ ነበር ይላሉ የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት። ለዚህም ማስረጃቸው በወቅቱ ስፖርቱ በቂ ትኩረት ይሰጠው እንደነበር በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ 50 የሚደርሱ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች እንደነበሩና በእነዚህ ክለቦች ውስጥ በርካታ ወጣቶች ታቅፈው ይሰለጥኑና ይወዳደሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮናው ከሁሉም የአፍሪካ ዞኖች በማጣሪያ ውድድር አንደኛ የወጡ ሀገራት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ በ7 የውድድር ዓይነቶችና በሁለቱም ጾታዎች (በነጠላ፣ ቡድን፣ ድብልቅ እና በጥንድ) ከ100 በላይ ተጫዋቾች የሚወዳደሩም ይሆናል። በ7 የውድድር አይነቶች በሚከወንበት በዚህ ውድድር ኢትዮጵያም በሰባት ወንድና በሰባት ሴቶች ትወከላለች፡፡ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን በ2024 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአዋቂዎች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ላይ ለሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ስለመስራቱ ደግሞ የሚገልጸው የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ነው፡፡
የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዬና ውድድር ላይ የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች ለውድድሩ ብቁ ለማድረግ በማሰብ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ከአለም አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋራ በጣምራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እውቁ አሰልጣኝ አሌክሲ የፍሬሞፍ በማስመጣት ከሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ጋር በማቀናጀት 16 ተጫዋቾችን አካትቶ ልምምዱን ከነሐሴ 26 ጀምሮ ለተከታታይ 8 ቀናት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ካሉ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ አቅም እንዳላቸው የገለፀው አሰልጣኝ አሌክሲ የፍሬሞፍ የማዘውተሪያ ስፍራ፣ የአሰልጣኝ፣ የጠረጴዛ ቴኒስ ማቴሪያሎች መሟላት እንዳለባቸው እና ሀገራዊ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ መኖር እንዳለባቸው አስተያየቱን ለግሷልም ተብሏል፡፡ ስልጠናውም በአለም አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ድጋፍ በአውሮፓዊው አሰልጣኝ አማካኝነት በንድፈ ሃሳብና በተግባር ለተከታታይ 9 ቀናት ለ16 የብሔራዊ ቡድን አባላት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች አህጉር አቀፍ ውድድር ላይ ተሳትፎ ያደረጉና ልምድ ያላቸው እንደመሆኑ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ዝግጁ ናቸው። በቀሪው ጊዜም የቴክኒክና ታክቲክ ስልጠና በመስጠት ለውድድሩ ዝግጅት እንደሚደረግ ጠቁሟል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ አክለውም በ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርትን በማነቃቃት የአፍሪካ ዋንጫን በማዘጋጀት፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ በመሆን ኳታር በምታዘጋጀው የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በትኩረት ይሰራል፡፡ የጠበቀ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድና በሀገር ውስጥ ውድድሮችን በማስፋት፣ የክለቦችን ቁጥር በመጨመር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድንን የሚወክሉና ተተኪ ስፖርተኞችን፣ ዳኞችንና አሰልጣኞችን ለማፍራት የተለያዩ የገቢ ምንጮችን በማፈላለግ በትኩረት ለመስራት እንደ ትልቅ ግብ ይዘን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ዋናው መሰረት የአገር ውስጥ ውድድር መሆኑን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴንስ ፌዴሬሽን፣ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የክለቦች ሻምፒዮና ውድድሮች ስለመካሄዳቸው ያስረዳሉ፡፡ ውድድሩ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ባሳለፍነው የካቲት የተከናወነ ሲሆን፣ ስድስት ያህል ብሔራዊ ክለቦች በውድድሩ ላይ ተሳትፈዋል። በጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በውድድሩ ከተሳተፉ ክለቦች መካከል የኢቲዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ስፖርት ክለብ፣ የኔነህ አዲስ ስፖርት ክለብ እና የአዲስ ከተማ ወወክማ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በበጀት እጥረት የሚፈተነው ስፖርቱ በቀጣይ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ ለስፖርት ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት እና ችግር ፈቺ የሆኑ የስፖርት ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ መሰረታዊ የተቋሙ ቀጣይ የቤት ስራዎች ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ለዚህም በውድድሮች ላይ ስፖርተኞችን መመልመል፣ ተሰጥኦ ያላባቸውን አካባቢዎች በመለየት ምልመላ ማካሄድና ወደ ተቋማት እንዲመጡ በማድረግ ስልጠና መስጠት በፌዴሬሽኑ እየተሰራ ያለ ዋነኛ ስራ ነው። ከ17 ዓመት በታች አዳጊዎችን እና ከ15 ዓመት በታች በማደራጀት በሙሉ ጊዜያቸው እንዲሰለጥኑ እንደሚደረግም አቶ ተስፋዬ ይገልጻሉ፡፡
በቀጣይ ሊሰራባቸው የሚገቡና በ2016 ከተስተዋሉ ችግሮች መካከል በየዕድሜ ገደቡ ቡድኖችን ማደራጀቱ መዳከሙ እና የኢትዮጵያ ሻምፒዮንስ ውድድር በ2016 በጀት ዓመት አለመካሄዱና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። በስፖርተኞች የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ጥሰቶች በወቅቱ አለመታረሙ፣ በብሔራዊ ቡድን አመራረጥ ዙሪያ የግልፅኝነት ችግሮች መኖራቸውን፣ ለዳኞች፣ ለአሰልጣኞችና ለፕሮጀክቶች የሚሰጠው ስልጠና ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ክለቦችን የማፍራት ስራ ዝቅተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሊስተካከሉ ይገባል ብለዋል፡፡
ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲይዝና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እና በተለይ በትምህርት ቤቶች ጠንካራ ውድድሮች ማካሄድ በትኩረት እንደሚሰራባቸው ፌዴሬሽኑ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን በ2024 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚያካሄደው የአዋቂዎች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በማዘጋጀቷ ልምድ ልውውጥ፣ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ለውድድሩ ከሚደረጉ ድጋፎች መካከል ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያልገባና በዓለም አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ላይ አገልግሎት የሚሰጥ ምንጣፍ፣ የመጫወቻ ጠረጴዛ፣ መከለያ፣ ኳስ እና ራኬት እንድታገኝ ዕድል እንደሚፈጥርም ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሲሚንቶ ላይ ተጫውተው ወደ ውጪ ሄደው ምንጣፍ ላይ ሲጫውቱ ውጤታማነታቸው ላይ የራሱ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ለውድድሩ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ጠቀሜታ እንዳለው ተመላክቷል፡፡ በሌላም በኩል ኢትዮጵያም በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በሀገራዊ ገፅታ ግንባታ እንዲሁም በማቴሪያል ድጋፍ ፋይዳው የጎላ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የ2024ቱ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ከሻምፒዮናው ጎን ለጎን የአለም አቀፍ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት የሚታደሙበት የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በፉክክሩ አሸናፊ የሚሆኑ ተጫዋቾችም አፍሪካን በመወከል በዓለም የጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ በሚካሄደው ሻምፒዮና አሸናፊ ለሚሆኑ ብድኖች የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት ያዘገጀ ሲሆን፣ በነጠላ ውድድር 1ኛ ለሚወጡ 5 ሺህ ዶላር፣ 2ኛ ደረጃን ለሚይዙ 2 ሺህ 500 ዶላር እንዲሁም 3ኛ የሚሆኑ 1 ሺህ 250 ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ