ለቢሾፍቱ ከተማ ለውጥና እደገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል:- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

You are currently viewing ለቢሾፍቱ ከተማ ለውጥና እደገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል:- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

AMN – ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም

ለቢሾፍቱ ከተማ ለውጥና እደገት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስተዋፅኦ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለቢሾፍቱ ኮርደር ልማት ተቋሙ ከባለሀብቶች እና የልማት አጋር ግለሰቦች ጋር በመተባበር ያስገነባቸውን የልማት ፕሮጄክቶችን ከከተማው ለተውጣጡ የባለሀብቶች ቡድን አስጎብኝተዋል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ከጉብኝቱ በኋላ ከባለሀብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት የቢሾፍቱ ከተማ እና አየር ኃይል የረዥም ዘመናት ቁርኝት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው በዚህ የጊዜ ሂደት ሁሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለከተማው ዕድገት የራሱን በጎ አሻራ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ቢሾፍቱ በሀገሪቱ ቁጥር አንድ የቱሪስት መዳረሻ ስማርት ሲቲ ለማድረግ በተጀመረው የኮርደር ልማት ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንቁ ተሳታፊ መሆኑን ያስታወቁት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለልማቱ የእስካሁኑ ስኬት ባለሀብቱ እና የልማት አጋር የሆኑ ግለሰቦች ላደረጉት ድጋፍ አመሰግነዋል፡፡

ይህ መልካም ተነሳሽነት በቀጣይም ለከተማዋ ዕድገት የተያዘው ራዕይ ከግብ አስከሚደርሰ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

አያይዘውም ከከተማ መስተዳድሩ ጋር በልማት’ በፀጥታ እና በሌሎችም ተያይዥ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብሮ እንደሚሰራና የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው በከተማው የተጀመሩ የኮርደር ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጨምሮ መላው የከተማው ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች እያደረጉት ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በከተማ መስተዳድሩ ስም አመስግነዋል።

ባለሀብቶቹ የከተማው ኮርደር ልማት እጅግ እየተፋጠነና መሆኑን ገልጸዉ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ጠቁመው ለልማቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለወደፊቱም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በዕለቱ የባለሀብቶች ቡድን አየር ኃይል ለቢሾፍቱ ከተማ ኮርደር ልማት እያሰራ ያለውን የልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተቋሙን ልዩ ልዩ ከፍሎች ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review