AMN – ጥር 14/2017 ዓ.ም
ለተረጋጋ ፖለቲካና ቀጣይነት ላለው የምጣኔ ሃብት ዕድገት አገራዊ መግባባት መፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለጸ።
ብሄራዊ መግባባት ላይ ያተኮረው ሁለተኛው የፓርላማ ዜጎች ፎረም ዛሬ ተካሂዷል።
በፎረሙ ላይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፖሊሲ አውጪዎች ፣ምሁራን እንዲሁም የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ብሄራዊ መግባባት ለአንድ አገር ሰላምና ልማት እንዲሁም የጋራ ማንነት ግንባታ ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑም ተነስቷል።

አገራዊ መግባባት ባልተፈጠረባቸው ሁኔታዎች የግጭት ተጋላጭነቱ እንደሚያይልና ለውጭ ጠላት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) ብሄራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና በሚል ባቀረቡት የውይይት መነሻ እንዳመለከቱት አገራዊ መግባባት ባልተፈጠረበት አገር ውስጥ የሚኖረው ፖለቲካ የተቃርኖ ነው።
የተረጋጋ የፖለቲካ ቀጣይነትና የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ለማረጋገጥ አገራዊ መግባባት መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በፎረሙ የብሄራዊ መግባባት ታሪካዊ መሰረቶች በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ያቀረቡት በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ ጥናትና ምርምር ኃላፊ አብዲዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር) ናቸው።
ሀገሪቱ ያሏት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ለብሄራዊ መግባባት መሰረቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የነበሩ ጥንካሬዎችን የበለጠ ማስቀጠልና ያልተዳሰሱትን ማካተት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) የሀገራዊ መግባባት ፈተናዎች በሚል የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው የውይይት መነሻ አቅርበዋል።
ሀገረ መንግስቱን የሚፈትኑ ጉዳዮች ላይ የማይታረቅ አቋም መያዝ፣ ርዕዮተ አለምን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፅንፈኝነት፣ የገነገነ መጠራጠርና የመንግስት ቅቡልነት ማጣት እንዲሁም የሀሰተኛ መረጃ መበራከት የብዙ ሀገራት የብሄራዊ መግባባት ፈተናዎች ናቸው ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ሁኔታና የተገዳዳሪ ሃይሎች ፍላጎት፣ የትምህርት ደረጃና የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና እንዲሁም የደህንነትና የፀጥታ ስጋት የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት ላይ ስጋት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና አገራዊ ምክክር አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ የማይካሄድ በመሆኑ በችግሮች ውስጥ ሆኖም የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አገራዊ መግባባት ህልውናን ለማስጠበቅና ለትውልዱ የተሻለ አገር ለማስረከብ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የመጀመሪያው የዜጎች የፓርላማ ፎረም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ አተኩሮ ከአንድ ወር በፊት መካሄዱ ይታወሳል።
የፓርላማ ዜጎች ፎረም በየወሩ ለሀገር በሚበጁ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የሚካሄድበት መሆኑ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡