AMN – ታኅሣሥ 24/2017 ዓ.ም
በቅርቡ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ ፡፡
ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለመሆን ጥያቄ ላቀረቡ አገራት በሂደት ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ኢንጂነር አሸብር የገለፁት።
ከታዳሽ የሀይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ስፍራን የያዘችው ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማቱም ይሆን ቀጣናውን ተጠቃሚ የማድረግ ጥረቷን ቀጥላለችም ብለዋል።
ለዚህም የታዳሽ ኃይል አማራጭን በተለይም ከውሃ፣ ነፋስ፣ እንፋሎትና የጸሃይ ብርሃን የማምረት ስራዎች በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በኃይል ስርጭትና ተደራሽነት ከምስራቅ አፍሪካ ባለፈ የአፍሪካ የኃይል ማዕከል ለመሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ይታወቃል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ኢንጂነር አሸብር እንዳሉት በኃይል ልማትና ተደራሽነት እንዲሁም ቀጣናዊ ተጠቃሚነት ረገድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በእስካሁኑ ሂደት ከጎረቤት አገራት ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው፥ በቅርቡ ለታንዛኒያ ለመሸጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መጠናቀቁን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከምታመነጨው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሃይል 90 በመቶውን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በማዋል 10 በመቶውን ደግሞ ለተለያዩ አገራት እያቀረበች መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም የኃይል ልማትና ተደራሽነት ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው።
በደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በኩል ከኢትዮጵያ የኃይል ተጠቃሚነት ጥያቄ መቅረቡን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ ጥናት ተደርጎና የሃይል ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ግንባታ ሲከናወን ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የኃይል ሽያጭ አገራትን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው፥ የልማት ስራውና ቀጣናዊ የኃይል ትስስሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የልማትና የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ለማሳካት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዘርፉ ልማት መሳካት የግሉ ባለሃብት ተሳትፎም እንዲታከልበት መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ እንደሚያሳየው በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ታውቋል።