AMN- መስከረም 10/2017 ዓ.ም
ለትግራይ ክልል በፌዴራል መንግስት ድጎማ የተገዛ የምግብ ዘይት ወደ ክልሉ ማጓጓዝ መጀመሩን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አብረሀት ዓንደሚካኤል እንደተናገሩት፤ ክልሉ 6 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያስፈልገው ሲሆን በዚህ ሳምንት ዘይቱን ከወደብ ወደ ክልሉ የማጓጓዝ ሥራ ተጀምሯል።
በአሁኑ ወቅት 82 ሺህ 400 ሊትር ዘይት ገብቶ ለህብረት ሥራ ማህበራት ለማከፋፈል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት መንግስት በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚያደርገው ድጎማ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የልማት ድርጅቱ ዋና ዓላማ ህብረተሰቡ መሰረታዊ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ገበያን ለማረጋጋት እንደሚያስችል አመልክተዋል።
በቀጣይም ዘይት፣ ስኳር እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን እንዲሁም ጤፍ በድጎማ ለማቅረብ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
መቀሌ ላይ የሚገኙ 32 ሸማቾች እና ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበራት የምግብ ዘይትን ጨምሮ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ለዘመን መለወጫ በዓል ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ማረጋጋት ሥራ መስራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡