ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል 400 ሁለተኛ ዙር ሰልጣኞችን ተቀበለ

You are currently viewing ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል 400 ሁለተኛ ዙር ሰልጣኞችን ተቀበለ

AMN – ጥር 1/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለሴተኛ አዳሪነት እና ለተለያዩ የማህበራዊ ችግሮች ተጋልጠዉ የነበሩ 400 እህቶች እና ሴት ልጆች ለሁለተኛ ዙር ስልጠና እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፣ በመጀመሪያ ዙር ስልጠና የወሰዱ ከ300 በላይ የሚሆኑ እህቶቻችን በ17 አይነት ዘርፎች የክህሎት እና ተሃድሶ ስልጠና ወስደዉ የሞያ ባለቤት ሆነው የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

በማህበረሰባችን ውስጥ ስር በሰደደ ኋላቀር አስተሳሰብ፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ፆታዊ ጥቃት እና ተጋላጭነት ምክንያት በእህቶቻችን እና ሴት ልጆቻችን ላይ የሚደርስ ማህበራዊ ስብራትን በመጠገን ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን የጀመርነውን ስራ በመደገፍ ከጎናችን የቆማችሁ የከተማችን ልበ ቀና ባለሃብቶችን፣ የቦርድ አባላት፣ በሞያችሁ እየደገፋችሁን ያላችሁትን እንዲሁም ራዕያችንን ወደ መሬት ለማውረድ የደከማችሁ የማዕከሉ አመራሮችና፣ ሰራተኞች እንዲሁም መምህራን በእህቶቻችን ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁም ብለዋል።

የሁለተኛ ዙር ሰልጣኝ የሆናችሁ እህቶቻችን የማዕከሉ ቆይታችሁ እራሳችሁን የምትለውጡበት፣ ለቤተሰቦቻችሁ እንዲሁም ለሌሎች መለወጥ አርአያ የምትሆኑበት እንዲሆን አደራ እያልኩ የሚሰጣችሁን ስልጠና በትጋት በመከታተል እንደ መጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች ስኬታማ እንድትሆኑ ጥሪ አቀርባለሁ ሲሉም አክለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review