ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በሁለተኛው ዙር በ17 የሙያ አይነቶች ያሰለጠናቸውን 380 ሰልጣኞች አስመርቋል።
በሁለተኛ ዙር ወደ ማዕከሉ ከገቡት 400 ሰልጣኞች መካከል 380 የሚሆኑት የተሰጣቸውን የብቃት ምዘና በማለፍ ለምረቃ መብቃታቸውም ተመላክቷል፡፡
በምረቃ መርሐ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበረሰቡ ውስጥ ሴቶችን ለችግር የሚያጋልጡ በርካታ አጋላጭ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ የኢኮኖሚ ችግር፣ የአመለካከት መዛነፍ እና ማህበረሰባዊ ስብራትን የመሳሰሉት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ በጋራ መቆምና መተባበር አለብን ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ይህንን ካደረግን ችግሩን ማቃለል ይቻላል ብለዋል፡፡
ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና የክህሎት ማዕከልን በማቋቋም እና በርካቶችን በማስተባበር እየሰራን ያለነውም ለዚሁ ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ ሴቶችን ማብቃት ጠንካራ ሀገርን የመስራት አካል በመሆኑ ሴቶች በኢኮኖሚው ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ልንሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
ማዕከሉ ሰልጣኞችን በማብቃት ለሁለተኛ ዙር በማስመረቅ ለውጤት እንዲበቃ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ለአንድ ወር የተሃድሶ ስልጠና የተከታተሉ ሲሆን፣ ለአራት ወራት ደግሞ የተግባራዊ የክህሎት ስልጠናዎችን በ17 የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሲከታተሉ እንደቆዩ እና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ወስደው ከ93 በመቶ በላይ ፈተናውን ለማለፍ መቻላቸው ተገልጿል።
ለሰልጣኞቹ ለሁሉም የስራ እድል መመቻቸቱም በመድረኩ ተገልጿል።
ማዕከሉ ለተያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ፣ በጎዳና ተዳዳሪነት፣ በወሲብ ንግድ፣ ከስደት የተመለሱ እና ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶችን ተቀብሎ የህይወት ክህሎት እና የሞያ ስልጠና በመስጠት ወደ አዲስ ህይወት የሚያሰማራ ሲሆን፣ በ3ኛ ዙር 1ሺ የሚጠጉ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉም ተመላክቷል።
በሰብስቤ ባዩ