ለአዕምሮ ጤና ምን ያህል ትኩረት ሰጥተናል?

You are currently viewing ለአዕምሮ ጤና ምን ያህል ትኩረት ሰጥተናል?

“ባለቤቴ ትሁትና ታታሪ ነበር። ሰርቶ ለመለወጥና ጓደኞቹ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ሲተጋ ቆይቷል፡፡ ሃሳቡ ግን ሳይሳካለት ቀረ፤ የአዕምሮ ታማሚም ሆነ:: የህመሙ መንስኤ ከአጎቱ ልጅ ጋር መርካቶ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ይሰሩ ነበር፡፡ ሆኖም በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ይህም እንዲናደድ፣ ለጤና ቀውስም እንዲዳረግ አደረገው” ሲሉ ወይዘሮ ዝናሽ ጥላሁን የባለቤታቸውን የአዕምሮ ህመም መነሻ ያሉትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡

ሁኔታው ባለቤታቸውን እንዲናደዱ፣ እንቅልፍ እንዲያጡ፣ ብዙ እንዲያወሩ፣ ተሳዳቢና ተጠራጣሪ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ እነዚህን ነገሮች መቋቋም ሲያቅታቸውም ወደ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወሰዷቸው፡፡ ከባድ የአዕምሮ ህመም እንደታመሙ ተነገራቸው። በህክምናው ክትትል ተደርጎላቸው ለውጥ አምጥተው ወደ ቤታቸው ቢመለሱም ቀድሞ ሲሰሩት የነበረውን ስራ መስራት አልቻሉም። በዚህ አማካኝነትም ቤት ያለስራ ተቀመጡ፡፡

“ቤት መቀመጡ እና ስራ መፍታቱ የድብርት ስሜትን ፈጠረበት፡፡ ‘ድብርቱ እንዲለቅቀኝ’ በማለት ጫት መቃም ጀመረ። መድሃኒቱንም በአግባቡ አለመውሰድ ጋር ተያይዞ በድጋሚ  የአዕምሮ ህመሙ አገረሸ። ይባስ ብሎ በአሁኑ ወቅት የተጠራጣሪነት ስሜቱ እየጨመረ ሄዶ ‘ልጆቹን ከየት አመጣሻቸው? የእኔ ልጆች አይደሉም’ የሚል ንግግር መናገር ጀምሯል፡፡ ይህ ለእኔ የማልወጣው ፈተና ነው የሆነብኝ፡፡ ህይወቴም በመሳቀቅና በፍርሃት የተሞላ ሆኖ ቀጥሏል፡” ሲሉ የአዕምሮ ህመም በታማሚው ላይ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብም ጭምር አሉታዊ ተፅዕኖው ከባድ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

ወይዘሮዋ በመልዕክታቸው ማንኛውም ሰው ታምሞ በህክምና ባለሙያዎች የሚታዘዝለትን መድሃኒት በአግባቡ ከወሰደ መፍትሄ ያገኛል፡፡ ያ ሳይሆን ከቀረ ግን ከህመሙ ጋር እስከ መጨረሻው ይኖራል ሲሉ መድሃኒትን በአግባቡ መውሰድ አመራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ባለቤታቸውን ምሳሌ በማድረግ ይናገራሉ፡፡

ከላይ እንደተገለጸው አይነት በአዕምሮ ህመም ምክንያት ለጤና እና ተያያዥ ጉዳቶች የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስለጉዳዩ በውል መረዳት፣ የባለሙያ ምክር መስማትና ሌሎች የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡

የህመሙ ምንነት

ዶክተር ክብሮም ሃይሌ በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስትና የህክምና ክፍሉ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ማብራሪያ፣ አንድ ሰው የአዕምሮ ጤና አለው የሚባለው የእለት ተዕለት ተግባሩን ሲያከናወን እና ሀላፊነቱን መወጣት ሲችል ነው፡፡ የአዕምሮ ህመም ደግሞ በአንድ ሰው ላይ የአስተሳሰብ መዛባት፣ የስሜት እንዲሁም የባህርይ መለዋወጥ ሲከሰት ወይም ሲኖር ነው፡፡ ከመታመሙ በፊት ካለው ባህርይ ለየት ያለ ሁኔታ ሲያሳይና ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆይ የአዕምሮ ጤና መታወኩ ማሳያ ነው፡፡

በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስትና የህክምና ክፍሉ ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ሃይሌ

በሌላ በኩል የአዕምሮ ህመም አንድ ሰው ከዚህ በፊት ሲያከናውነው በነበረው የእለት ተዕለት ተግባሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድርበትና ማከናወን ሳይችል ሲቀር ነው። የሰውን ባህሪ የሚወስነው ዋናውና አንዱ ነገር አስተሳሰቡ ነው፡፡ በሚያስበውም መሰረት ይመራል፡፡ ከወትሮው የተለየ አስተሳሰብ ሲኖርበት ባህሪው ይቀያየራል፡፡ “ሰዎች ያሴሩብሃል፣ ይከታተሉሃል” የሚል አስተሳሰብ በአዕምሮው ውስጥ ከተከሰተ ከሰዎች የመራቅ፣ የመሸሸግ፣ ባህሪ በማስከትል ስራ እንዳይሰራ ያደርገዋል፡፡ ስሜቱም ለፍርሃት፣ ለመጠራጠር፣ ለጭንቀት እንዲሁም ለድብርት ይዳርገዋል፡፡

መንስኤዎቹ

እንደ ዶክተሩ ገለጻ፣ የአዕምሮ ህመም መንስኤዎች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ስነ- ህይወታዊ መንስኤዎች (biological causes) ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህም በዘር የአዕምሮ ህመም ካለበት ልጆቹ ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም የሚከሰተው በአዕምሮ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች (ኬሚካሎች) መዛባት ነው፡፡

ሌላኛው ስነ-ልቦናዊ መንስኤዎች (Psychological causes) ናቸው፡፡ እነዚህ መንስኤዎች ደግሞ ከአስተዳደግ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ሆነው እስከ አዋቂነትም የሚከተሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- በልጅነት ጊዜ በቂ እንክብካቤ አለማግኘት፣ በቤት ውስጥ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ አብዝቶ መጨነቅ፣ የቤተሰብ መበተን፣ በተረበሸ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ፣ የቅርብ ሰዎችን በሞት ማጣት… ምክንያት የሚመጣ ውጥረት፣ ሀዘን ወይም ብስጭት፣ ፍርሃት፣ ከልጅነት ጀምሮ የተለያዩ አካላዊ፣ ጾታዊ ወይም ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ውስጥ ማለፍ፣ ወዘተ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡

ማህበራዊ መንስኤዎች (social causes) የሚባለው ደግሞ ሶስተኛው መንስኤ ሲሆን፤ ይህም የገንዘብ እጥረት፣ ስደት፣ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ሱስ አምጭ ነገሮችን መጠቀም፣ የእኔ የሚሉትና ችግራቸውን የሚያካፍሉት ሰው አለመኖር፣ መገለል፣ ብቸኝነት፣ ‘ሰው ሊጎዳኝ ይችላል’ የሚል የጥርጣሬ ስሜት፣ የጭንቀት ስሜት ይጠቀሳሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ማህበራዊ ችግሮች ሲገጥማቸው ጊዜያዊ መፍትሄ ብለው በሚያስቡት መጠጥ መጠጣት እንዲሁም ጫት መቃም ሱስ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም የአዕምሮ ታማሚ ይሆናሉ፡፡

የህመሙ አይነቶች

የአዕምሮ ህመም አይነቶች ብዙ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በዋናነት ግን በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ይናገራሉ። አንደኛው አዘውትሮ የሚከሰት የአዕምሮ ህመም አይነት ነው፡፡ ይህ የህመም አይነት ሲከሰት የሚያሳያቸው ምልክቶች፣ ቀላል ወይም ከባድ ድብርት፣ የጭንቀት ህመም፣ በምርመራ የማይገኙ በሰውነት ውስጥ ህመም ያለ የመምሰል ስሜት ነው፡፡

ሁለተኛው የአዕምሮ ህመም ከባድ የአዕምሮ ህመም አይነት ነው፡፡ ይህ ራስን እስከ ማጥፋት የሚያደርስ ከባድ የሆነ የድብርት ህመም ነው፡፡ በዋናነትም ተፅዕኖ የሚያሳድረው የአስተሳሰብ መዛባት ላይ ነው፡፡ የሚያሳያቸው ምልክቶችም አንድ ጊዜ በጣም የመደሰት ሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም የማዘን ስሜት፤ ነገሮችን ከእውነታው ወጣ ብሎ መረዳት፣ ሁሉም ሰው እነሱን እንደሚጎዷቸው ማሰብ፣ አብዝቶ ተጠራጣሪ መሆን፣ ሁሉም ሰው በራሱ ጉዳይ ሲያወራ በእሱ ጉዳይ የሚያወራ መምሰል፣ ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት አለመቀበል፣ ለሌላ ሰው የማይሰማ ድምፅ ለእነሱ መሰማት፣ ይህም የመረበሽና እረፍት ማሳጣት፣ መበሳጨትና መልስ የመስጠት ስሜት ከባድ የአዕምሮ ህመም እንዳለ ማሳያዎች ናቸው ይላሉ፡፡

99 በመቶ የሚሆኑት የአዕምሮ ህመሞች ቀላል ሲሆኑ፤ አንድ በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከባድ የአዕምሮ ህመም ነው የሚሉት ዶክተሩ፤ ከባዱ የአዕምሮ ህመም ትንሽ ይሁን እንጂ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ቤት ውስጥ ከባድ የአዕምሮ ህመም ታማሚ ካለ ቤተሰቡ በሙሉ ሰላም አያገኝም፤ ስራ ሰርቶ ለመመለስም አዳጋች ነው፡፡ ቤተሰቡ በስጋትና በጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ምክንያት የሚሆንም ነው፡፡

የአዕምሮ ህመም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚከሰት ሲሆን፤ በአብዛኛው ከ19 እስከ 25 ዓመት የሚከሰት ነው፡፡ ይህ እድሜ አንድ ተማሪ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚገባበት፣ ተመርቆ ስራ የሚጀምርበት አለፍ ሲልም እየሰራ ያለበት ሊሆን የሚችልበት በመሆኑ አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ነው፡፡ ይህም ታማሚውን ከስራ ውጭ በማድረግም ይሁን በቤተሰቡ ላይ ጫና በመፍጠር የሃገርን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ነው፡፡

በህፃናት እድሜ ላይ የሚያጋጥሙ የአዕምሮ ህመሞች ከአፈጣጠር ጋር አብረው ያሉ ናቸው፡፡ አንድ ህፃን አዕምሮው በአግባቡ ባለማደጉ ምክንያትና ነርቭ ላይ በሚከሰት ችግር የአዕምሮ እድገት ውስንነት ሊገጥመው ይችላል፡፡ የሚከሰተውም በእናታቸው ማህፀን እያሉ መደረግ ያለበት ክትትል ሳይደረግላቸው በመቅረቱና እናትየዋ የሚያነቃቁ ነገሮችን ባለማድረጓ የሚከሰት ነው፡፡

ህክምናው ምንድ ነው?

የአዕምሮ ህመም ህክምና የሚወሰነው ህመሙን ባመጡት ምክንያቶች ነው እንጂ አንድ ወጥ የሆነ ህክምና የለውም ያሉት ዶክተር ክብሮም፤ ታማሚው የገጠመው ችግር ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊ እንዲሁም ስነ ህይወታዊ መሆኑን ቅድሚያ የመለየት ስራ ይሰራል፡፡ ይህንንም ለመለየት ቢያንስ ከእሱ ጋር የህክምና ባለሙያው ለአንድ ሰዓት ያህል በማውራት እና ወደኋላ ያሉትን ታሪኮች በማወቅ ነው፡፡ ከዚያም ችግሩ ስነ ህይወታዊ ከሆነ የመድሐኒት (ኪኒን) ህክምና፣ ስነ ልቦናዊ ከሆነ የምክር አገልግሎት የመስጠት እንዲሁም ማህበራዊ ችግር ከሆነ ደግሞ ችግሮቹ እንዲቀረፉ በማድረግ ነው፡፡

ስለ አዕምሮ ህመም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር አድልዎ እና መገለል እንደሆነ የሚያነሱት ስፔሻሊስቱ፤ የአዕምሮ ህመም ችግር ሲፈጠር ብዙዎች እንደማይድን በማሰብ ታማሚውን የመሸሽ እና የማግለል አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የህክምና ባለሙያውና ተቋሙም የመገለል ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ የአዕምሮ ታማሚዎች ቢኖሩም ወደ ህክምና ቦታ የሚመጡት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የአዕምሮ ህመም በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት፣ እንደማንኛውም ህመም ሊታከም የሚችል ነው፡፡ ይህ የተዛባ አመለካከት ተቀርፎ ወዲያውኑ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ታማሚው አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ ቢደረግለት ህመሙን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች እንደታመሙ አያውቁም፤ ህመማቸውን የሚያውቁላቸውና አንደበት ሊሆኗቸው የሚችሉት ማህበረሰቡ፣ ቤተሰብና የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት በማገዝ፣ በማሳከም በመደገፍ ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ከተማ በአዕምሮ ህመም ዙሪያ ብዙ ጥናቶች ይጠናሉ፡፡ ነገር ግን ወጥነት የሌላቸውና የተቆራረጡ እንዲሁም ህብረተሰቡን ሳይሆን ተቋምን ብቻ የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለዚህም እንዲህ ሆነ ለማለት ያስቸግራል የሚሉት ዶክተሩ፤ ተቀራራቢ የሆኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከአዕምሮ ህመሞች ከባድ የአዕምሮ ህመም አንድ በመቶ፣ የድብርት ህመም 5 በመቶ፣ በህፃናት ላይ የሚከሰተው (ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘው) ከ10 እስከ 12 በመቶ ይደርሳል ብለዋል።

ከህመሙ ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

አዕምሮ የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ህይወቱን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችለው ሚዛን በመሆኑ የአዕምሮ ህመም ቀላል ተደርጎ ሊታይ አይገባም። በዚህም የአዕምሮ ጤናችንን እንዴት መንከባከብና መጠበቅ እንዳለብን ሲያብራሩ፤ የመጀመሪያው ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ሲሆን፤ ከስጋ ይልቅ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ፤ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከስራ በኋላ በቂ የሆነ እረፍት ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ከተለያዩ ሱሶች ከማጨስ፣ አልኮል ከመጠጣት እና ከመሳሰሉት ነገሮች ራስን መጠበቅ ነው፡፡

ሁለተኛው የአዕምሮ ጤናን ለመጠበቅ የምንከተላቸው ነገሮች በስራም ይሁን በትምህርት ወይም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የሚያጋጥሙንን ግጭቶች ቶሎ መፍታት መቻል ተገቢ ነው፡፡ መናደድ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ከንዴቱ በኋላ ራሳችንን እንዴት ማረጋጋት እንዳለብን ማወቅ፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ማህበራዊ ግንኙነት ማስተካከል አስፈላጊ ነው፡፡ በሃገራችን አንዳንድ ግጭቶች፣ መፈናቀል፣ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን መስማት፣ ስራ አጥነት የመሳሰሉት ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡ ይህም የስነ ልቦና ችግር እንዲሁም ድህነትን በማምጣት  ለአዕምሮ ህመም ያጋልጣል፡፡ ይህ እንዳይሆን መረዳት መደጋገፍ አንዱ ለአንዱ መቆምን ማዳበር አስፈላጊ  እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

አንድ ሰው ለአዕምሮው የሚያደርገው እንክብካቤ ለቆዳው ከሚያደርገው እንክብካቤ ማነስ መቻል የለበትም፡፡ ለቆዳችን የተለያዩ ነገሮች እናደርጋለን፤ ለአዕምሮ ግን ትኩረት አናደርግም፤ ከጥሩ ነገር ይልቅ መጥፎ ነገሮችን እንወስዳለን፡፡ ይህ መሆን የለበትም፤ ነገሮችን በበጎ ጎን ማየትን ልምድ ልናደርገው ይገባል ሲሉ አዕምሮም እንደሌላው የሰውነታችን ክፍል እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ፡፡ 

የአእምሮ ጤና  ቀን በዓለም  አቀፍ  ደረጃ እ.ኤ.አ ጥቅምት  10  ቀን  2024 (መስከረም  30  2017 ዓ.ም) “በስራ  ቦታዎች  ቅድሚያ  ለአእምሮ  ጤና፤ ጊዜው  አሁን ነው”  በሚል  መሪ  ሀሳብ  ተከብሮ  ውሏል፤  ዓላማውም ምቹና  ጤናማ  የስራ  አካባቢን  መፍጠር አንደኛው  የአእምሮ  ጤና  መጠበቂያ  መንገድ ነው የሚል ነው።

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review