
AMN – ጥር 19/2017 ዓ.ም
በፈረንጆቹ 1963 የተመሠረቱው የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ስም ሲነሳ ሁሌም የሚታወሱ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች መኖራቸው እሙን ነው ።
መሪዎቹ የአፍሪካ አንድነት ፣ ነፃነትና ትብብርን ለማጎልበት ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ናቸው ።
ለአህጉሪቱ ባላቸው ቀና ራዕይ እና ተፅእኖ ፈጣሪነታቸውም ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያው ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ፣ የጋናው ፕሬዝዳንት ኩዋሜ ኑክሩማ፣
የታንዛኒያው ጁሊዬስ ኔሬሬ፣ የኬኒያው ጆሞ ኬኒያታ እና የግብፁ ገማል አብዱልናስር በህብረቱ የምሥረታ ሂደት ስማቸው ከፊት የሚጠቀሱ ባለውለታዎች ናቸው።
የእያንዳንዳቸው ጥንካሬና ስብዕናም በተለያየ መልክ ይገልፃል ።
ዐፄ ኃይለ ስላሴ ያላቸው የዲፕሎማሲ ብልሀት፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላቸ ክብርና ለአፍሪካ ሉዓላዊነት የነበራቸው ቆራጥነት ከሚጠቀሱ ጥንካሬዎቻቸው መካከል ጥቂቶቹ ናቸው ።
የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያውን የምስረታ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እንዲያካሂድ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸው ፣ለአፍሪካ መሪዎች የአመራርነትን እና የአንድነት ጥንካሬ ተምሳሌት እንደነበሩ ይነሳል።
የነፃነት ተምሣሌት የሆነችው እና ለመላ የአፍሪካ ሀገራትም ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብሩ መነሳሳት የፈጠረችውን ኢትዮጵያ ያስተዳደሩና ነፃነቷንም ያከበሩ መሆናቸው ዐፄ ኃ/ሥላሴን ከአፍሪካ ህብረት መሥራች መሪዎች መካከል ልዩ ያደርጋቸዋል።

የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኙ እና የጋናው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኩዋሜ ሌላው ስማቸው የሚወሳ ጠንካራ አፍሪካዊ መሪ ናቸው።
ባለራዕይ ፣ ተደማጭ፣ ፓን አፍሪካኒስት እና አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት አለባት የሚል ፅኑ አቋም የነበራቸው መሆኑ ጥንካሬያቸውን አጉልቶ ያሳያል።
በተለየ መልኩ የሚታወቁበትን የፓን አፍሪካኒዝም አጀንዳ ቅርፅ ማስያዛቸው እና ለህብረቱ ምስረታ የአንበሳውን ድርሻ መወጣታቸው ከአበርክቶአቸው መካከል ይገኛል።
በህብረቱ የመወያያ አጀንዳ የነበረውና አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል ወይም “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ” በሚለው ተፅዕኖ ፈጣሪ ንግግራቸው ዛሬም ድረስ ይታወሳሉ።
በምሁርነታቸው እና የመርህ ሰው በመሆን የሚገለፁት የታንዛኒያው ጁሊዬስ ኔሬሬ በአፍሪካ የአንድነት ድርጅት ምስረታ ጉዞ አሻራ ካኖሩት መካከል ሌላኛው ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሪ ናቸው ።

የአፍሪካ ነፃነት እንቅስቃሴን በተለይም የደቡባዊ የአፍሪካ ክፍልን በመደገፍ እና የአፍሪካን አንድነት በማጎልበት ረገድ የተወጡት ሚና ከፍተኛ ነበር ።
ይበልጡንም ራስን መቻል እና ግጭቶችን በሠላም መፍታት በሚለው መርሀቸው ታሪክ ያስታውሳቸዋል።
ለቀጣናዊ ትብብር እና ከነፃነት ማግስት ሊኖር ስለሚገባው ሀገረ መንግስት ግንባታ አፅንኦት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ የሚታወቁት ደግሞ የኬኒያው ጆሞ ኬኒያታ ናቸው።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር የተወጡት ቁልፍ ሚና ከማይዘነጉት ሥራዎቻቸው መካከል ተጠቃሹ ነው ።
ስትራቴጅስት መሆናቸው የሚነገርላቸው እና የአፍሪካን የነፃነት እንቅስቃሴ የደገፉ እንዲሁም በአፍሪካና አረብ መካከልም አንድነትን ለማምጣት ጉልህ ሚና ያበረከቱት የግብፁ የቀድሞ መሪ ገማል አብዱልናስርም ተጠቃሹ አፍሪካዊ መሪ ናቸው ።

የቅኝ ግዛትን በመታገል አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ያዋደዱ በመባልም ይታወሳሉ።
ሁሉም መሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ ዐፄ ኃ/ሥላሴና ክዋሜ ንክሩማ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ የነበራቸው ቀጥተኛ ሚና እና ራዕይ ያለው አመራርነት አበርክቶአቸውን የላቀ ያደርገዋል።
ታቦ ምቤኪ ፣ ኦሊሴጎ ኦባሳንጆ፣ አብዱላዚዝ ቡቶፍሊካ እና ሙአመር ጋዳፊም ከፈረንጆቹ 2000 በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስያሜን “አፍሪካ ህብረት ወደ ሚለው በመቀየር እና ሀሳቡንም በመደገፍ የሚታወቁ መሪዎች ነበሩ።
በማሬ ቃጦ