ለኮሪደር ልማት ተነሺዎች 8ሺ የሚደርሱ ቤቶች ተገንብተው ነዋሪዎች እንዲገቡ ተደርጓል፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN ኅዳር -30/2017 ዓ.ም

በኮሪደር ልማት ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች 8ሺ የሚደርሱ ቤቶች ተገንብተው ነዋሪዎች እንዲገቡ መደረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ለካዛንቺስ አካባቢ የልማት ተነሺዎች የተገነባው የገላን ጉራ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት እና የመኖሪያ መንደር ተመርቋል።

አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ ለማድረግ ቃል ገብተን ወደ ስራ ስንገባ መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን የሰውን ኑሮ ለማሻሻል ጭምር ትኩረት ሰጥተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ልማቱ ሲሰራ ነዋሪዎች አስቸጋሪ ከነበሩ የመኖሪያ አካባቢዎች ተነስተው ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ ቤቶች እና መኖሪያ አካባቢዎች እንዲዘዋወሩ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልጸዋል።

ገላን ጉራ የመኖሪያ መንደር 1ሺ 200 የቀበሌ ቤት ነዋሪ የነበሩ አባወራዎች እና እማወራዎች ከነቤተሰቦቻቸው ወደ ተዘጋጁላቸው መኖሪያዎች የገቡ ሲሆን ህጋዊ ውል ሳይኖራቸው በቀበሌ ቤቶች ተለጣፊ ቤቶችን ገንብተው ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችም ደረጃቸውን ወደ ጠበቁ መጠለያዎች እንዲገቡ በመደረጉ በጥቅሉ 1ሺ 500 የሚደርሱ አባወራዎች እና እማወራዎች ከነቤተሰቦቻቸው የገቡበት ነው።

ለልማት ተነሺዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች መኖሪያ ቤት እና መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የተናገሩት ከንቲባዋ ለግል ባለ ይዞታዎች ከ12 ቢሊየን ብር በላይ ካሳ መከፈሉን እና ከ100 ሄክታር በላይ ምትክ መሬት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የገላን ጉራ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት እና የመኖሪያ መንደር ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ከባቢን ለመፍጠር የሚያስችሉ የመንገድ፣ የትራንስፖርት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች የህጻናት መጫዎቻ ፣ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፣ የህጻናት ማቆያ፣ የምገባ ማዕከላት፣ የከነማ መድሃኒት ቤት፣ የዳቦ እና እንጀራ ማምረቻዎች ፣ የንግድ መደብሮች እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው።

የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ በሁለት ወራት ውስጥ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላደረጉ እና በገንዘብ ለደገፉ አካላትም ከንቲባ አዳነች ምስጋና አቅርበዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review