ለወጣቶች ብርታት የሆኑ ፊልሞች

You are currently viewing ለወጣቶች ብርታት የሆኑ ፊልሞች

ፊልሞች ወጣቶችን የማዝናናት፣ የማስተማር እና ለትልቅ ለውጥ የማነሳሳት ሃይል አላቸው። በወጣቶች ላይ ያላቸው ተጽእኖ ደግሞ ግልጽና የማይካድ ነው። ምክንያቱም ፊልሞች የወጣቶችን ሀሳብ፤ ህልም እና ምኞት የመቅረጽ ችሎታ አላቸው፡፡

በፊልሞች ላይ የሚታዩ ገጸ ባህርያት የህይወት ውጣውረዶችን በማሸነፍ፣ ህልማቸውን የሚያሳኩ እና በአለም ላይ በጎ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ከሆኑ ወጣቶችም ይህን የመማርና የመተግበር እድላቸው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡

የፊልም ኢንዱስትሪዎች የጽናት ታሪኮችን፣ የማይታለፉ የሚመስሉ መሰናክሎችን ለማሸነፍ ውስጣዊ ጥንካሬ እና ቁርጠኝነት ያላቸው ገጸ ባህርያትን በፊልሞቻቸው አማካኝነት ተደራሽ ሲያደርጉ ወጣቶች በዚህ በጎ ተጽእኖ ስር ይወድቃሉ፡፡ እነሱም ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው፣ ችግርን መሻገር እንዳለባቸው፣ መፍትሄ ፍለጋ ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ያምናሉ፡፡

ፊልሞች በራስ የመተማመን ስሜትን፣ ርህራሄን እና በአለም ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ያላቸውን ፍላጎት እንዲያዳብሩ ይረዷቸዋል። በመሆኑም ፊልሞች የቀጣዩን ትውልድ አእምሮ እና ልብ መቅረጽ፣ ትልቅ ህልም እንዲኖራቸው፣ ጠንክረው እንዲሰሩ እና በራሳቸው አቅም እንዲያምኑ የማበረታታት አቅም አላቸው።

የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በመጪው ሰኞ የሚከበረውን “አለም አቀፍ የወጣቶች ቀን”  ምክንያት በማድረግ ወጣቶች ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ፣ ራሳቸውን እንዲለውጡና ወገኖቻቸውን እንዲጠቅሙ የማድረግ ሃይል አላቸው ከሚባሉ ፊልሞች ውስጥ ጥቂቶችን በአጭሩ አዘጋጅቷል። መረጃዎች የተወሰዱት ከዩዝ አስፓይሪንግ መጽሄት፣ ማይሆፒኮርስ እና ሙቪዌብ ከተሰኙ ገጸ ድሮች ነው፡፡

ሶል ሰልፈር

በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ሶል ሰልፈር ፊልም

“ሶል ሰልፈር” የተሰኘው ፊልም የተሰራው እ.ኤ.አ. በ2011 ነው፡፡ ፊልሙ ቢታንያ ሃሚልተን በተሰኘች ሴት እውነተኛ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ፊልሙ የአካል ጉዳት ያለባቸው ወጣቶች አላማቸውን ከማሳከት፣ ህልማቸውን ከመኖር ምንም እንደማያግዳቸው ያሳያል፡፡

ቢታንያ ሃሚልተን  በ13 ዓመቷ በባህር ላይ በሚደረግ የስፖርት ውድድር ወቅት በሻርክ ተነክሳ የግራ እጇን ሙሉ በሙሉ አጣች፡፡ ይህ ግን ህልሟን ከመኖርና ተወዳድሮ ከማሸነፍ አላገዳትም፡፡ በርካታ ውድድሮችን ተፎካክራ ማሸነፍ ቻለች፡፡ ለሌሎችም ተምሳሌት ሆነች።“ሶል ሰልፈር” ፊልም እውነተኛ ታሪክ ነው፣ እጇን በሻርክ ጥቃት ያጣችው ወጣት ሴት፣ በድፍረት ሁሉንም ውድድሮች በማሸነፍ እንደገና ሻምፒዮን ለመሆን ስትበቃ ይተርካል። ይህች ወጣት የአካል ጉዳተኛ ሴት ወጣቶችን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በቆራጥነትዋ እና በጥረቷ አርአያ ለመሆን በቅታለች፡፡ ፊልሙም የሚያሳየው ይህንኑ ነው።

ዘ ኢንተርንሺፕ

ዘ ኢንተርንሺፕ ፊልም እና ተዋናዮቹ

ይህ ፊልም የተሰራው እ..አ. በ2013 ነው። “ዘ ኢንተርንሺፕ” ከስራ ገበታቸው ላይ የተቀነሱ ወጣት ሰራተኞች ላይ ያተኮረ ፊልም ነው። ታዋቂዎቹ ኦወንዊልሰን እና ቪንስቮን በዚህ ፊልም ላይ ተውነውበታል፡፡ ወጣቶቹ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ለውጥ ምክንያት ከስራ ከተቀነሱ በኋላ በጎግል ካምፓኒ ስራ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትና ይህም ጥረታቸውን ተቀባይነት ሲያገኝ ያሳያል፤ ወጣቶችም ተስፋ ባለመቁረጣቸው፣ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቃቸው በጎግል በመስራት ስኬታማ ሆኖ ለመቀጠልም እድል አግኝተዋል። ፊልሙን ተወዳጅ የሚያደርገው ደግሞ የኮሜዲ ዘውግ ያለው፣ ቀላል እና እያዝናና የሚያስተምር መሆኑ ነው፡፡ ሙቪዌብ የተሰኘው ገጸ ድር “ዘ ኢንተርንሺፕ” የተሰኘው ፊልም ላይ በሰራው ዳሰሳ ወጣቶች ተስፋ እንዳይቆርጡ የሚያደርግ፣ የሚያበረታታ እና እያዝናና ለትልቅ ለውጥ የሚያነሳሳ ብሎታል፡፡

ቱ ሴቭ ላይፍ

ወጣቶችን እያዝናና ከሱስ እንዲወጡ የሚያስተምረው የቱ ሴቭ ላይፍ ፊልም

ጄክ የተሰኘ አንድ ወጣት ጓደኛው በሱስ እና መጠጥ ውስጥ ቆይቶ ራሱን ካጠፋ በኋላ ነበር ህይወቱ የተቀየረው፡፡ እናም ፊልሙ አንድ ወጣት የሌሎችን ሕይወት ለማዳን እና ጓደኞቹን እንዲሁም በዙሪያው የሚገኙ ወጣቶችን ለመርዳት እስከ ምን ድረስ መጓዝ እንደሚችል የሚያሳይ እና ለበጎ ተግባር የሚያነሳሳ ነው፡፡

ጄክ በህይወቱ ያጣውን የቀድሞ የልጅነት ጓደኛው ከሱስ ለማውጣት እና ከሞት ለማተረፍ የሰራው ስራ አለመኖሩ ጸጸተው፡፡ ባለፈው ከመጸጸት ይልቅ ለወደፊቱ መስራት እንዳለበትም ውሳኔ ላይ ደረሰ። በዚህም የብዙ ወጣቶችን ህይወት ለማዳን ቆርጦ ተነሳ። አዳዲስ ጓደኞችን በማቅረብ እና በመርዳት ወደ ትክክለኛው የህይወት መስመር ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረትና ይህም ሲሳካለት ፊልሙ ያሳያል፡፡

ጥቂት ስለ አለም አቀፍ የወጣቶች ቀን

አለም አቀፍ የወጣች ቀን በየአመቱ በፈረንጆቹ ነሐሴ 12 ይከበራል፡፡ ዘንድሮም እለቱ በመጪው ሰኞ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቦ ይውላል፡፡ በዓሉ የሚከበረውም  ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለወጣቶች ጉዳዮች  ትኩረት  እንዲሰጥት እና  ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ለማስታወስ፣ ለመዘከርና ለበጎ ለውጥ ለመጠቀም የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።  ቀኑ የወጣቶችን ድምጽ ለመስማት፣ ለለውጥ ያላቸውን ተነሳሽነት ለማሳደግ እንዲሁም ትርጉም ያለው፣ ሁለንተናዊ እና ፍትሃዊ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ እድል ይሰጣል ተብሎ ይታመናል። በዓሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ  ከጸደቁ አለም አቀፍ ቀኖች አንዱ ነው። እለቱ በአለም አቀፍ በዓልነት የጸደቀው በፈረንጆቹ ታህሳስ 17 ቀን 1999  ነበር፡፡

ምንጭ፡-ኖሌጅ ሃብ ገጸ-ድር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review