ለዘመናት የፀና ወዳጅነት፤ የተጠናከረ ትብብር

You are currently viewing ለዘመናት የፀና ወዳጅነት፤ የተጠናከረ ትብብር

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ጉብኝታቸው ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፣ “ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን በሚያጠናክሩ ሰፋ ያለ መጠነ ርዕይ ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየት ምንጊዜም አስደሳች ነው” ብለዋል።

አክለውም “ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል እና በታኅሳስ ወር በአዲስ አበባ ከነበረን ውይይት ቀጥለን ስላካሄድነው ፍሬያማ ውይይት ምስጋናዬን እገልጣለሁ። ትብብራችን በብዙ ጠቃሚ ዘርፎች የቀጠለ ሲሆን የንግድ ትስስሮቻችንን የበለጠ ማሳደግ ከቅድሚያ የትኩረት ማዕከሎቻችን አንዱ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ለመሆኑ የፈረንሳይና የኢትዮጵያ የትብብር ታሪክ ምን ይመስላል? ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በተለያየ ጊዜ ያደረጓቸው ውይይቶች ምንድን ናቸው? መሪዎቹ በተለያየ ጊዜ የሚደርጓቸው ጉብኝቶች ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጠናከር ምን አበርክቶ አለው?

የሁለቱ ሀገራት የትብብር ታሪክ

የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን የተሻገረ ነው። ሁለቱ ሀገራት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1897 ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1904 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ የወዳጅነት ቢሮ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ መከፈቱ ለግንኙነታቸው መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። 127 ዓመታትን የተሻገረው ይህ ግንኙነት በትምህርት፣ በባቡር መሰረተ ልማት፣ በሙዚቃና ፊልም፣ በዲፕሎማሲ፣ በንግድ እና በተለያዩ መስኮች ላይ ያተኮረ ነው። የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ግንኙነት ከመንግስታት በተጨማሪ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን መሰረት ያደረገ ጭምር ነው፡፡

ዘመናትን የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ትብብር አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቅርብ ዓመታት ያደረጓቸውን ውይይቶች በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

መሪዎቹ በተለያዩ ጊዜያት የመከሩባቸው ጉዳዮች

የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ከሚያሳዩ ጉዳዮች መካከል የመሪዎች ጉብኝት እና ውይይት አንዱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአውሮፓ ሀገራት የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ አንደኛዋ መዳረሻቸው ፈረንሳይ  እንደነበረች ይታወሳል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል ሁለቱን ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ አንድ በሚያደርጓቸው አጀንዳዎች፣ በጸረ ሽብርና  በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ መስራት የሚሉት ነጥቦች ይገኙበታል፡፡

ከዚያም የጉብኝት ልውውጡ ቀጥሎ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት መምጣታቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፈረንሳይን ከጎበኙ ከወራት በኋላ ፕሬዝዳንት ማክሮን በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው በርካታ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተው ተመልሰዋል፡፡

ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል። በወቅቱ ከተፈረሙ ስምምነቶቹ መካከል ፈረንሳይ ለላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርስ እድሳት የሙያና የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግበት ማዕቀፍ ይጠቀሳል። ማክሮን በወቅቱ የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በአካል በመገኘት መጎበኝታቸው ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ኢንቨስትመንት እና ሌሎች  የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መሪዎች ተስማምተዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም ድጋሚ ተወያይተዋል፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “ከወንድሜ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሁለትዮሽ ግንኙነት እና አኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ ስለ ነበረን ፍሬያማ ውይይት ምስጋናዬ ይድረስ” ብለዋል። በሀገሮቻችን መካከል ያለው የዳበረ ግንኙነት ለቀጣይ ትብብር ጠንካራ መሰረትን የጣለ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሁለቱ መሪዎች በአካል ብቻም ሳይሆን በስልክም ውይይቶችን አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በጥር ወር 2015 ዓ.ም በሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ በስልክ ተወያይተው ነበር፡፡ በወቅቱ በእርስ በርስ መተማመን እና መከባበር ላይ የተመሰረተው የኢትዮ-ፈረንሳይ ግንኙነት 125 ዓመታትን ማስቆጠሩን የሚያስታውስ መልዕክት በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ማስፈራቸው አይዘነጋም።

ታህሳስ 2017 ዓ.ም ደግሞ ፕሬዚዳንት ማክሮን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባ የመጡበት ወቅት ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “ወንድሜና የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፉት ስድስት ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ” በማለት መልዕክት አጋርተው ነበር፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ በመጠናከር ላይ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው በመነጋገር ላይ  የተመሰረተ እና  የዓለም አቀፍ ሕግን እና መርሕን የተከተለ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም ይህንኑ ሕግ እና መርሕ የተከተለ በመሆኑ ፈረንሳይ ጥያቄውን እንደምትደግፍ አመልክተዋል። ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄም ፈረንሳይ አስፈላጊውን ድጋፏን እንደምታደርግ ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ይሳካ ዘንድም ፈረንሳይ ያላሰለሰ ጥረት እንደምታደርግም ቃል ገብተዋል፡፡

ኢዜአ በ2015 ዓ.ም የሰራው ዘገባ እንደሚያሳየው በርካታ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡና ወደ ፈረንሳይ ስትልክ ፈረንሳይ በበኩሏ የትራንስፖርት ቁሳቁሶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ በዋናነት ትልካለች። በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገሮች በመካከላቸው ያለው የኢኮኖሚ ትስስር እየጎለበተ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ የሁለቱ መሪዎች የጉብኝት ልውውጦች ወሳኝ ሚና የተጫወተ ነው ማለት ይቻላል። የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉብኝትም ለሀገራቱ ትብብር ተጨማሪ መሰረት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review