ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቻይና የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ጋር ተወያየ

You are currently viewing ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቻይና የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ጋር ተወያየ

AMN-ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም

ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቻይና የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ጋር ተወያይቷል።

የልዑካን ቡድኑን የሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ከዲፓርትመንቱ ምክትል ሚኒስትር ሊ ሚንሽያንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት የፓርቲ ለፓርቲ፣ የመንግስት ለመንግስት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ሃሳቦች መነሳታቸውንና በቀጣይ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ መደረሱን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

አቶ አደም ፋራህ ቻይና እና ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በማውሳት በሁሉም ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት መመስረታቸውን ማብራራታቸውም ተመላክቷል።

በተጨማሪም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱ በልምድ ልውውጥ፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በሌሎች የአቅም ግንባታ ድጋፎች ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ወደፊትም ይበልጥ አብረው ለመስራት ብልጽግና ፓርቲ ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸውም እንዲሁ።

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ምክትል ሚኒስትር ሊ ሚንሽያንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን የማንኛውም ወቅት ጽኑ ወዳጅነት(all weather partnership) በሚባል ደረጃ ማድረሳቸውን መግለጻቸው ተመላክቷል።

ይህንን አስጠብቆ ለመቀጠል ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽም ሁለቱ ፓርቲዎች የገነቡት የረጅም ጊዜ ትብብርም የመንግስት ለመንግስት ግንኙነቱን በሚያጠናክር ደረጃ መድረሱን አንስተዋል።

አቶ አደም ፋራህ መንግስት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እየሰራቸው ስላሉ ስራዎችና ስለተገኙ ውጤቶች፣ በፓርቲ እየተከናወኑ ስላሉ የአቅም ግንባታና ሪፎርም ጥረቶች እና እየተገኙ ስላሉ ፋይዳዎች እንዲሁም ስለአካባቢያዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበው ሰፊ ውይይት መደረጉም በመረጃው ተጠቅሷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review