ለገና በዓል ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡባቸው ባዛሮች በሁሉም ክፍለ ከተሞች በቂ ዝግጅት አድርገዋል፡-አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ

AMN – ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም

ለገና በዓል ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡባቸው ባዛሮች በሁሉም ክፍለ ከተሞች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የገና በዓል የምርት አቅርቦትን በሚመለከት የቅድመ ዝግጅ ስራው ያለበትን ደረጃ እና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ በከተማዋ ምርት አቅርቦትን ከሚመሩና ከሚከታተሉ ባለድርሻአካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ በመደበኛነት መቅረብ ከሚገባቸው ምርቶች በተጨማሪ በቀጣይ ሳምንታት የሚከበረው የገና በዓል የምርት ፍላጎትን የሚጨምር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በሁሉም የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት የሰብል ምርቶች፤ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ የቁም እንስሳት፤ዶሮ፤ እንቁላል እና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽዎ ምርቶችን በስፋት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ በሚቻልባቸው አግባብ ላይ በስፋት ውይይት ተደርጓል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ቀደም ብሎ በበዓላት ወቅት እንደሚደረገው ሁሉም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በየገና በዓል ሲቃረብ ሰፋ ላሉ ቀናት ምርቶችን ያቀርባሉ ብለዋል፡፡

በመጨረሻዎቹ የበዓሉ ዋዜማ ቀናት በማዕከል ያሉ ሴክተር ተቋማት፣ አምራቾች እና ምርትን በጅምላ የሚያስመጡ አከፋፋዮች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡባቸው ባዛሮች በሁሉም ክፍለ ከተሞች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የምርት አቅርቦቱ የተሻለ እና እጥረት ያለመኖሩን ጠቅሰው ይህንኑ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በቢሮው የንግድ ግብይትና ገበያ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ጥበቡ ሁሉም የገበያ ማዕከላት እና የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በምርት አቅርቦቱ ላይ በርትተው በመስራት የምርት ዕጥረት እንዳይፈጠር እና የዋጋ መጨመር እንዳያጋጥም ጥብቅ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ በየደረጃው ካለው አመራር እና ባለሙያ የሚጠበቅ መሆኑን ማንሳታቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review