ለገና በዓል ንፅህናውን የጠበቀና ጤንነቱ የተረጋገጠ እርድ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅት ተጠናቋል፡-የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት

AMN – ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም

ለገና በዓል ንፅህናውን የጠበቀና ጤንነቱ የተረጋገጠ እርድ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጅትን ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር’ የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ጋር በጋራ በመሆን የገና በዓል ዝግጅትን በተመለከተ ለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከ4ሺ በላይ የሚሆኑ የዳልጋ ከብቶች ዕርድ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የድርጅቱ የኢንፎርሜሽንና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል ገልፀዋል፡፡

ለኅብረተሰቡ ንፅህናውን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በፍጥነት እና በተቀላጠፈ መልኩ ለማቅረብ የእርድ መሳሪያዎች እንዲሁም የስጋ መጓጓዣ መኪናዎች ዝግጁ መሆናቸውን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የሰው ኃይል እጥረት እንዳያጋጥም ድርጅቱ ከ1 ሺህ 100 በላይ ጊዜያዊ ሰራተኞች መቅጠሩን ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

በመዲናዋ የሚከሰቱ ሕገ-ወጥ የእንስሳት እርድን ለመከላከል ከደንብ ማስከበርና ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቅሰው ኅብረተሰቡም ጥቆማ በማድረግ እንዲተባበር ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል።

በበዓሉ በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ ዘንድ ሰፊ የስጋ ፍላጎት የሚኖርበት ወቅት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ በሚገኙ ልኳንዳ ቤቶች በተመመጣጣኝ ዋጋ በቂ የስጋ አቅርቦት እንደሚኖርና ህብረተሰቡ ከበዓሉ እለት ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

በቤትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ እርዶች ከእንስሳት ወደ ሰው ለሚተላለፉ በሽታዎች ተጋላጭ ስለሚያደርጉ፥ ህብረተሰቡ በቄራ ብቻ የታረደ ስጋ በመመገብ የራሱን እና የቤተሰቡን ጤና እንዲጠብቅ በማለት ሃላፊዎቹ አሳስበዋል።

በመሀመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review