AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ ለህዝብ ቃል በገባው መሰረት ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ከ700 በላይ የጤና ተቋማት መገንባታቸውን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ለህዝብ ቃል ከገባቸው የማህበራዊ ልማት መስኮች አንዱ የጤና አገልግሎትን ማሻሻል ነው።
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በርካታ እመርታዎችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
የማህበረሰቡን ጤና በመጠበቅ ጤናማ ትውልድ በማፍራት በኢኮኖሚ ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚ እና ተሳታፊ እንዲሆን ሰፋፊ ስራ በመስራት በርካታ ድሎች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል።
በዋናነት የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸው በዚህም ላለፉት 31 ዓመታት የቆየውን መከላከልን ብቻ መሰረት ያደረገው ፖሊሲ መሻሻሉን ጠቁመዋል።
አዲሱ ፖሊሲ በዋናነት ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን የመጀመሪያው መከላከልን በማጠናከር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከልን ባካተተ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን እንስተዋል።
ሁለተኛው አክሞ የማዳን አቅምን ከፍ ማድረግ መሆኑን ገልጸው ይህም ከህክምና መሳሪያ እና ከጤና ተቋማት ጀምሮ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሶስተኛው የፖሊሲው ትኩረት የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮችን መቋቋም የሚችል የጤና ስርዓት መገንባት ነው ብለዋል።
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ የጤና ተቋማት መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ ከዚህም ውስጥ ከ300 በላይ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የጤና ኬላዎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከ400 በላይ የጤና ጣቢያዎች መገንባታቸውን እና ትልልቅ አቅም ያላቸው 81 ሆስፒታሎች በተለያዩ ክልሎች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።
አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ከስድስት በላይ የስፔሻሊቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ዶክተር ደረጀ አክለውም በሀገር ውስጥ የህክምና መሳሪያዎች እና መድሀኒት የማምረት አቅምም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም ከፍተኛ መጠን ያለው የህክምና ግብዓት ከውጭ እንደሚገባ ገልጸው አሁን መሰረታዊ በሚባል ደረጃ በሀገር ውስጥ እየተተኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ 36 በመቶውን የመድሃኒትና የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።
የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተወሰደው እርምጃም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተጠቃሽ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።
በአጠቃላይ ከለውጡ ወዲህ በዘርፉ በርካታ ውጤት የተገኘባቸውና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ የጤና ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም ጤናማ ትውልድ የመገንባት ሥራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡