AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለማችን በአንድ ዓመት ብቻ 57 ሚሊዮን ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ ይመረታል፡፡
በዚህ ፈታኝ የብክለት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ለችግሩ እልባት ለማበጀት ያስችላል የተባለውን ስብሰባ በደቡብ ኮሪያ እያካሄደ የሚገኘው፡፡
የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን “ማንኛውም ሰው በመኖሪያ አካበቢም ሆነ በአረንጓዴ ሥፍራ የፕላስቲክ ቆሻሻ ማየት አይወድም” በማለት ገልጸዋል፡፡
ለፕላስቲከ ብክለት መፍትሔ ለማበጀት ያለመ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ላለፉት አራት ዓመታት የተካሄደ ቢሆንም በፍላጎትና በግብ ደረጃ ሰፊ ልዩነቶች የተስተዋሉበት እንደነበር ይገለጻል፡፡
በስብሰባው ላይ ከሀገራት ልዑካን በተጨማሪ የፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ሳይንቲስቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችም እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
ስብሰባው ስኬታማ ሆኖ የሚጠናቀቅ ከሆነ በ2022 የተጠነሰሰው ህጋዊ ማዕቀፍ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በኖርዌይ እና ሩዋንዳ የሚመራው የ66 ሀገራት ስብስብ እና የአውሮፓ ህብረት የፕላስቲክ ዲዛይን፣ ምርትና ፍጆታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ በማድረግ በዓለም ዙሪያ ያለውን ሁሉንም ፕላስቲክ ለመቆጣጠርና ማብቂያ ለማበጀት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
ደሴቶች ላይ የተመሰረቱ ሀገራት በበኩላቸው፤ ከፍተኛ መጠን ባለው የፕላስቲክ ብክለት ስለሚቸገሩ የተሻለ ትኩረት እንደሚሹ ጥሪ ማቅረባቸውን አፍሪካ ኒውስ ነው የዘገበው፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!